ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን 'ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ' ስርዓትን በማስተዋወቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

ኢዜአ፤ ጥር 2/212 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን 'ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ' ስርዓትን በማስተዋወቅ ላይ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብና አዘገጃጀት አዋጅ ትግበራን ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ የሚመክር የመገናኛ ብዙኀን የጋራ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ከኢዜአ፣ ከኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት የተዉጣጡ አካላት ተሳትፈዋል።

ከተቋቋመ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በሁሉም የግል፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተፈፃሚ የሚሆነውን የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብና አዘገጃጀት አዋጅ ትግበራን ያስፈፅማል።

የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሂክመት አብደላ እንዳሉት በዓለም ላይ ከ160 በላይ አገራት አዲሱን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ተግባራዊ እያደረጉ ነው።

ይህ ዘመናዊ አሰራር ከግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ፍትሀዊነት አንጻር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልፀው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራትም ይህን አሰራር ገቢራዊ ማድረግ ያሻቸዋል ብለዋል።

የፋይናንስ ስርዓት ጤናማነትን ለማረጋገጥ የሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጠው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያም ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብን የተመለከተ አዋጅ በ2006 ዓ.ም ማፅደቋን ተናግረዋል።

አዋጁን የሚያስፈፅመው የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቶ በበርካታ ተቋማት ላይ መተግበሩን፣ አሰራሩን ለማስተዋወቅም በርካታ ተግባራት ማከናወኑንም አክለዋል።

ያም ሆኖ ግን አሰራሩን በሁሉም መንግስዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በማስፈጸም የህዝብ አመኔታ ያለው መረጃ በአገሪቱ የፋይናንስ ሪፖርት እንዲተገበር ሰፊ ስራ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በዚህ ረገድ በዘርፉ ህግና ስርዓት ተጠብቆ አዋጁ እንዲተገበር ቦርዱ ከሚዲያ ጋር መስራት እንደሚፈልግ ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ሂክመት አመልክተዋል።

የመገናኛ ብዙኀን ተቋማትም ለአዋጁ ተፈጻሚነትና ውጤታማነት ከቦርዱ ጋር በመስራት አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሀድጎ በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ኃላፊነት በመጠቀም የፋይናንስ ሀብት ግልፅነት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ አሰራሩ ከፀደቀ ዓመታት ቢቆጠሩም ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ አሰራር በሚፈለገው ደረጃ አለመታወቁንና በሁሉም ተቋማትና ዘርፎችም ተፈፃሚ አለመሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ይህ ሁኔታ እንዲለወጥ የመገናኛ ብዙሃን አሰራሩን በማስተዋወቅ ረገድ በስፋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ወይዘሮ ለምለም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም