ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነገ በስፔን የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ይሳተፋሉ

ኢዜአ፤ጥር 1/2012 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም በስፔን ሁለት የተለያዩ ከተሞች በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ይሳተፋሉ።

የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮቹ የሚካሄዱት የስፔን ከተማ በሆኑት ኤልጎይባር እና ቫሌንሺያ ነው።

በኤልጎይባር ከተማ በሚካሄደው የሁዋን ሙጉኤርዛ የአገር አቋራጭ ውድድር በወንዶች የ10 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር አትሌት ሚልኬሳ መንገሻና አትሌት ታደሰ ወርቁ ይሳተፋሉ።

ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች የአትሌቲክስ ህይወቱን የጀመረው አትሌት ሚልኬሳ በአሁኑ ሰአት በጎዳና ላይ የሩጫ ውደድሮች ትኩረቱን አድርጓል።

እ.አ.አ በ2019 በዴንማርክ የኮፐንሀገን የግማሽ ማራቶን 1 ሰአት ከ1 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱን ማስመዝገብ ችሏል።

አትሌት ሚልኬሳ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም በ36ኛው የጃን ሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር የኦሮሚያ ክልልን በመወከል ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ይሄንኑ ውጤት ተከትሎ አትሌቱ ባለፈው ዓመት በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተካሄደ 43ኛው ዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ በወጣት ወንዶች የ8 ኪሎ ሜትር ውድድር 23 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል።

አትሌት ሚልኬሳ በነገው በየሁዋን ሙጉኤርዛ የአገር አቋራጭ ውድድር የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያመለክታል።

ሌላኛው አትሌት ታደሰ ወርቁ እንደ አትሌት ሚልኬሳ በ36ኛው የጃን ሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ሀዋሳ ከነማን በመወከል በ8 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች ውድድር ላይ ተሳትፎ አራተኛ ወጥቶ ነበር።

በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተካሄደው 43ኛው ዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ ውድድር በወጣት ወንዶች የ8 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ሚልኬሳን ተከትሎ ሁለተኛ መውጣቱ አይዘነጋም።

በወንዶች የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያና ስፔን ተወዳዳሪዎች ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በሴቶች የ7 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ውድድር ታዋቂዋ የኬንያ አትሌት ሄለን ኦቢሪ  የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን ያገኘች ሲሆን የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ እንደነበረችም የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ አስፍሯል።

ለ77ኛ ጊዜ የሚካሄደው የሁዋን ሙጉኤርዛ ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ውድድር በዓለም አትሌቲክስ እውቅናና ፈቃድ የተሰጠው ውድድር ነው።

ውድድሩ የሚካሄደው የቀድሞዋ የስፔን ታዋቂ መካከለኛ ርቀት አትሌት ሁዋን ሙጉኤርዛ መታሰቢያነት ነው።

በሌላ በኩል ነገ በስፔን ቫሌንሺያ ከተማ በሚካሄደው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በወንዶች አትሌት ጫላ ረጋሳ ይሳተፋል።

እ.አ.አ በ2014 በኔዘርላንድ ሌይደን ከተማ በተካሄደ የአትሌቲክስ ውድድር በ800 ሜትር ሩጫ የአትሌቲክስ ህይወቱን የጀመረው አትሌት ጫላ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ትኩረቱን ወደ ጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች አድርጓል።

የባለፈው ዓመት ውድድርን 27 ደቂቃ ከ23 ሴኮንድ አሸናፊ የነበረ ሲሆን የቦታውን ክብረ ወሰን ማሻሻል ችሏል።

በነገው ውድድርም የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን ካገኙ አትሌቶች መካከል አንዱ ሆኗል።

ኬንያዊው አትሌት ሮኔክስ ኪፕሩቶ ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት መውሰዱን የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያመለክታል።

በሴቶቹ ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ሼሊያ ቼፕኪሩይ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝታለች።

የቫሌንሺያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በዓለም አትሌቲክስ የነሐስ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም