የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የፊፋ ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ነገ ከዩጋንዳ አቻው ጋር ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የፊፋ ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ነገ ከዩጋንዳ አቻው ጋር ያደርጋሉ
ኢዜአ ጥር 01/2012፡- የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የፊፋ የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ነገ ጥር 2 ቀን 2012 ዓም ከዩጋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል። 7ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት 2013 ዓ.ም በህንድ አስተናጋጅነት እንደሚካሄድ ይታወቃል። በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍ የሚደረጉ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ይጀምራሉ። ነገ ጥር 2 ቀን 2012 ዓም በካምፓላ ስታር ታይምስ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻው ጋር ይጫወታል። በአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ ለጨዋታው ዝግጅት ይረዳው ዘንድ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ከታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል። ካሉት 23 ተጫዋቾች አምስቱ ተቀንሰው 18 ተጫዋቾችና ሌሎች ሰባት ልዑካን ተጨምረው ትናንት ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓም ወደዩጋንዳ ያቀኑ ሲሆን ጨዋታው በሚደረግበት ሜዳ ልምምዳቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ብሔራዊ ቡድኑ ያደረገው ዝግጅት በጣም አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይ ረዘም ያለ የዝግጅት ጊዜ እንዲኖርና አሰልጣኞችም ተጨዋቾችን በደምብ የሚመዝኑበት ሁኔታ እንዲፈጠር አሳስበዋል። የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም ይደረጋል። በዚህ ጨዋታ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ካሸነፉ ከቅድመ ማጣሪያ ወደ መጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ያልፋል። በህንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 7ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ። ሰሜን ኮሪያ ሁለት ጊዜ ደቡብ ኮሪያ፣ ስፔን፣ ፈረሳይና ጃፓን አንድ አንድ ጊዜ የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫን አሸንፈዋል። በተጨማሪም ኮስታሪካና ፓናማ በጋራ በሚያዘጋጁትና ለ10ኛ ጊዜ በሚካሄደው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የኢትዮጵያ ከ20 በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም ከብሩንዲ አቻው ጋር ብሩንዲ ላይ የመጀመሪያ የቅድመ-ማጣሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። በአሰልጣኝ ፍሬው ሃይለገብርኤል የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ ለጨዋታው ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታዲየም እያደረገ ይገኛል።