ኢትዮጵያ ከፊቷ የተደቀኑ አሳሳቢ ፈተናዎችን አልፋ የብልፅግና መንገድን ትይዝ ዘንድ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተደቀኑ አሳሳቢ ፈተናዎችን አልፋ የብልፅግና መንገድን ትይዝ ዘንድ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ተባለ
ኢዜአ ጥር 1/2012 ኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግሮችን አልፋ ሁለንተናዊ ዕድገት ይኖራት ዘንድ ሁሉም ሰው መትጋት እንደሚገባው የአገሪቱን መፃኢ ሁለንተናዊ ሁኔታዎች በማገናዘብ ወደፊት የሚኖሩ ተስፋና ተግዳሮቶችን የተነተነው ቡድን አባላት አሳሰቡ። 'ዴስቲኒ ኢትዮጵያ' የተባለ ድርጅት ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት ውስብስብ ችግር መፍትሔ ይሆናል በማለት በዚሁ ዘዴ አማካኝነት የተነተነውና የአገሪቱን መፃኢ ተስፋ፣ እድልና ተግዳሮት የተመለከተው የሁኔታ ጥናት 'ሴናሪዮ' በቅርቡ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ይኸው 'ትራንስፎርማቲቭ ሴናሪዮ ፕላኒንግ' የተሰኘው የአስተዳደር ስልት ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት የተወሳሰበ ችግር ውስጥ የገቡ የዓለም አገራትን ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከችግሮቻቸው ታድጓቸዋል ተብሏል።
ይህ ስልት በተለይ ደግሞ ልዩነትን መነሻ ያደረጉ ቁርሾዎችን ታከው በሕዝቦች መካከል የቅራኔ መነሻ የሆኑት ችግሮች ማቅለያ መንገድ ሆኖ በደቡብ አፍሪካ ጭምር ፍቱን መፍትሄ መሆኑም ተጠቁሟል።
በ2032 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሊከሰቱ የሚችሉ ናቸው የተባሉና የፉክክር ቤት፣ አጼ በጉልበቱ፣ ሰባራ ወንበርና ንጋት የተባሉ ስጋትና ተስፋን ያዘሉ የሁኔታዎች ትንተና በ'ዴስቲኒ ኢትዮጵያ' ይፋ ተደርጓል።
አራቱ የሁኔታ ትንተናዎች የሚወክሉት የአገሪቱ ስርዓተ መንግስት በአቅመ ቢስ አስተዳዳሪ ወይም በአምባገነን አሊያም ኃላፊነት በማይሰማው ኃይል ስር ይወድቃል፤ እነዚህን ሁኔታዎች መከላከል ከተቻለ ግን ሰላምና እድገትን ጨምሮ ሁሉም በጎ ነገር የሰመረላት አገር እውን ትሆናለች የሚሉትን ነው።
ከተንታኝ የቡድኑ አባላት መካከል ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉት አቶ ቀጄላ መርዳሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሁሉም ሊረባረብለት የሚገባው ንጋት በሚል የቀረበውን የመጨረሻውን ሁኔታ ላይ ነው ይላሉ።
ቡድኑ በአገሪቷ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ነው የሁኔታዎች ትንተናውን (ሴናሪዮ) ያመላከተው ሲሉም ገልፀዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግምባር (ኦነግ) ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጭምር የሆኑት አቶ ቀጄላ ''ዕድሉን አግኝቶ ቡድኑ ውስጥ መሳተፍ በራሱ ትልቅ ነገር ነው'' ይላሉ።
በቡድኑ ውስጥ ከማህበራዊ እስከ ፖለቲካ፤ ከንግድ ተቋማት እስከ መገናኛ ብዙሃን ባለድርሻ አካላት የተወከሉበት እንደነበርም ገልጸዋል።
እሳቸውም የቡድኑ አባልነታቸው ከፖለቲካ ወገን መሆኑን ጠቅሰው ''ሶስቱ አሳሳቢ ሴናሪዮዎች እውን እንዳይሆኑ'' በትጋት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ቡድኑ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የዴሞክራሲ፣ የሰላምና ጸጥታ፣ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ተንትኖ አቅጣጫ ያስቀመጠ ነውም ብለዋል።
በነዚህ ዘርፎች ውስጥ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ዜጋ አወንታዊ ሚናውን ካልተወጣ በ'ንጋት' የተመሰለው ሴናሪዮ እውን ሊሆን አይችልም ሲሉም አሳስበዋል።
ሌላዋ የቡድኑ አባልና በማሕበረሰብ ልማት ዘርፍ እየሰሩ የሚገኙት ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው ''ሴናሪዮ ግምታዊ ምልከታ ሳይሆን ሳይንሳዊ ትንተና ነው'' ይላሉ።
ከምንም በላይ ስጋትን መቀነሻ መንገዱ "ተቀራርቦ ማውራት፣ መወያየት፤" እንደሆነም በማከል።
ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዓመታት የሚኖራት የተበላሸ ታሪክ ሳይሆን ሁሉንም ዜጎችን የሚጠቅም ገጽታና ሁለንተናዊ እድገት ይኖራታል ነው ያሉት።
እርሳቸው እንደቡድኑ አባልነታቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በአገሪቷ ላይ እያንዣበበ ያለውን ስጋት ለሌሎች የማሳወቅ ስራ እንደሚሰሩ ገልጿል።
''ሁሉም ሰው የስጋቱን ከባድነት ከተረዳ፤ ስጋቱን ወደ ተሻለ ተስፋ ለመለወጥ ይረዳል'' በማለት ያስረዳሉ ወይዘሮ ፍሬዓለም።
ሂደቱ አሁን በአገሪቷ ላይ አንዣቦ ያለውን ስጋት መቀነስ የሚያችል መሆኑ የሚረጋገጠው የንግግር ባህላችን ጭምር ሲሻሻል ነውም ብለዋል።