ቀጥታ፡

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች በሠላም ስምምነቱ የተግባቡባቸውን ሀሳቦች በመተግበር ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት አለባቸው

ኢዜአ ጥር 1/2012 የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ በሠላም ስምምነቱ ከመግባባት የደረሱባቸውን ሀሳቦች በመተግበር ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት እንደሚገባቸው ተገለጸ። ኢትዮጵያና ሱዳንን በመሰረተ ልማት ማስተሳሰር ላይ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅም ተመልክቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋንን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። በውይይታቸው በሁለትዮሽ፣ በክልላዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች መስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ 33ኛ የመሪዎች ጉባዔ የሠላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።ሁለቱ ወገኖች የፈረሙት ስምምነት የቀደሙትን የሠላም ስምምነቶች ያጠቃለለም ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በስምምነቱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሁለቱ ወገኖች ተግባራዊ ለማድረግ የተስማሙባቸውን ነጥቦች ተፈጻሚ ለማድረግ 50 ቀናት እንደቀራቸው ገልጸዋል። ሁሉም ተደራዳሪ ወገኖች ልዩነታቸውን በማጥበብ በቀሪዎቹ ቀናት የሠላም ስምምነቱን ለመተግበር ቁርጠኝነታቸውን በተግባር ማሳየት ይገባቸዋል ብለዋል። በደቡብ ሱዳን የተጀመረው የሠላም ስምምነት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጸዋል። ሁለቱ አገራት ያላቸውን ቅርርብ ያህል በመሰረተ ልማት ያልተሳሰሩ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ገዱ በዚህ በኩል ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግም ነው ያመለከቱት። በደቡብ ሱዳን በኢንቨስትመንት ስራ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል። በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኢጋድ ሊቀመንበርነት ዘመኗ በደቡብ ሱዳን ሠላም እንዲሰፍን ለተጫወተችው ጉልህ ሚና አመስግነዋል። የደቡብ ሱዳን መንግስትም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሠላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት ይሰራልም ብለዋል። የደቡብ ሱዳን አጠቃላይ የሠላም ስምምነት የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ አምባሳደር ጀምስ ማብራሪያ መስጠታቸውን የሚኒስቴሩ መግለጫ አትቷል። በቀጣናው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ትስስር ለመመስረት ክልላዊ ፕሮጀክቶች ተለይተው ወደ ተግባር እንዲገቡ ደቡብ ሱዳን የበኩሏን እንደምትወጣም ገልጸዋል። በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ደህንነት እንዲጠበቅ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አምባሳደሩ መግለጻቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም