የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ ስልጠና ተጀመረ

ኢዜአ ጥር 1/2012 በኢትዮጵያ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል። በአካዳሚው የስፖርት ጅምናዚየም ዛሬ የተጀመረው ስልጠና ከደቡብ ኮሪያ የወርልድ ቴኳንዶ ቹንግ ዶ ኳን ፌዴሬሽን በመጡት አሰልጣኞች በሆኑት በግራንድ ማስተር ሺን ቹንግ ዶ ኳንና በረዳታቸው ሼመስ ኦኔል አማካኝነት ነው። ስልጠናን የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽንና ኢትዮ-ፋይት ናይት ትብብር በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በስልጠናው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ዳን ያላቸው አሰልጣኞች ናቸው። በስልጠናው ላይ 86 አሰልጣኞች እየተሳተፉ ናቸው። የኢትዮ - ፋይት ናይት መስራችና ኃላፊ ማስተር ዳግማዊ ወርቅነህ እንደተናገረው፤ ስልጠናው ለአሰልጣኞች የስፖርቱን ቴክኒኮች ይበልጥ ለማወቅ እንዲረዳቸው ያደርጋል። በአሁኑ ወቅት በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ውስጥ ያሉ ቴክኒኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣታቸውን ጠቁመው፤ በዚህ ስልጠና አሰልጣኞቹ ከግራንድ ማስተሮች ጥሩ እውቀቶችን እንደሚቀስሙም ተናግረዋል። ከዚህ በፊት የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ ስልጠና ለማግኘት ወደ ውጭ አገር ሲሄዱ እንደነበር ገልጸው፤ እስከአሁን አሰልጣኞች በጋራ በመሆን የወርልድ ቴኳንዶ የስፖርት ቴክኒኮችን እውቀት የሚያገኙበት ሁኔታ ሳያገኙ መቆየታቸውን አመልክተዋል። ዛሬ የተጀመረው ስልጠና ለሁሉም ኢትዮጵውያን አሰልጣኞች ተሳታፊ እንዲሆኑ እድል ፈጥሯል። የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች ከስር ላሉት አሰልጣኞችም ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ሁኔታም ስልጠናው እንደሚፈጥር ነው ማስተር ዳግማዊ ያስረዱት። ደቡብ ኮሪያዊው ግራንድ ማስተር ሺን ቹንግ ዶ ኳን ዘጠነኛ ዳን  ረዳታቸው አየርላንዳዊው ግራንድ ማስተር ሼመስ ኦኔል ስምንተኛ ዳን ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይም ከአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጋር የአሰልጣኞችና የተወዳዳሪዎች ስልጠናዎች እንዲሁም ውድድሮች ለማዘጋጀት እቅድ መያዙንም አክለዋል። የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሃይሉ ጉተታ የስልጠናው መዘጋጀት ወርልድ ቴኳንዶን ጨምሮ ሌሎች የማርሻል አርት ስፖርቶች እንቅስቃሴ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ዓለም አቀፍ የወርልድ ቴኳንዶ ስልጠናዎች አንድ አሰልጣኝ በየጊዜው ያለበትን ደረጃ በማሻሻል የተሟላ እውቀት እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።   ስልጠናው ለስፖርቱ እድገት ያላው ፋይዳ ታይቶ በአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን እና በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን እውቅና እንደተሰጠው ተናግረዋል። በቀጣይም የአሰልጣኞችና ተወዳዳሪዎችን አቅምና ደረጃ የሚያሳድጉ ስልጠናዎች እንደሚዘጋጁን በጥር መጨረሻም ለተወዳዳሪዎች የተዘጋጀ ስልጠና እንደሚዘጋጅም ጠቁመዋል። ግራንድ ማስተር ሼመስ ኦኔል ስልጠናው የውድድር ቴክኒኮች ላይ ሳይሆን፤ ከውድድር በፊት በሚያስፈልጉ መሰረታዊ ቴክኒኮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት እንዲያድግ በታዳጊዎች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተው፤ በስፖርቱ ያደጉ አገሮችም ተሞክሯቸው ይሄ እንደሆነም አንስተዋል። "ያለ ታዳጊዎች በአንድ አገር ውስጥ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርትን ማሰብ በፍጹም አይቻልም" ያሉት ግራንድ ማስተር ሼመስ ኢትዮጵያ በታዳጊዎችና ሴቶች ላይ አተኩራ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል። የወርልድ ቴኳንዶ ቹንግ ዶ ኳን ፌዴሬሽን እ.አ.አ በ2021 ተመሳሳይ ስልጠና በኢትዮጵያ እንደሚሰጥና ስፖርቱ በአገሪቷ እንዲያድግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አክለዋል። ዓለም አቀፍ የወርልድ ቴኳንዶ የአሰልጣኞች ስልጠና እስከ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ይቆያል። የደቡብ ኮሪያው የወርልድ ቴኳንዶ ቹንግ ዶ ኳን ፌዴሬሽን በአፍሪካ ይሄን አይነት ስልጠና ሲሰጥ የመጀመሪያው  ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የወርልድ ቴኳንዶ የመጨረሻው የዳን ደረጃ ዘጠነኛ ዳን ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም