መንግስታዊ ጫና፣ የተዛባ ትርክትና ታሪክን የማጠልሸት ተግባር ለኢትዮጵያ ታሪክ ዕድገት ተግዳሮት ሆነውታል-ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስታዊ ጫና፣ የተዛባ ትርክትና ታሪክን የማጠልሸት ተግባር ለኢትዮጵያ ታሪክ ዕድገት ተግዳሮት ሆነውታል-ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ
ኢዜአ ጥር 1/2012.. መንግስታዊ ጫና፣ የተዛባ ትርክትና ታሪክን የማጠልሸት ተግባር ለኢትዮጵያ ታሪክ ዕድገት ተግዳሮት መሆናቸውን በአዲስ አባበ ዩኒቨርሲቲ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ተናገሩ። ፕሮፌሰሩ 'የጋራ ታሪኮች ላይ ተግባበቶ ወደፊት መራመድ ይገባል፤ ታሪክ ትምህርት ቤት እንጂ እስር ቤት መሆን የለበትም' ብለዋል። የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በየወሩ መጨረሻ የሚያካሂደው ወርኅዊ መድረክ 'የኢትዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ፣ ዕድገቱና ተግዳሮቱ' በሚል ርዕሰ ጉዳይ ትናንት ማምሻውን ተካሂዷል። በውይይት መድረኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋው የታሪክ ምሁር ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና በስራ ባልደረባቸው በፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ አወያይነት ነበር የተመራው። ታሪክ በቀዳማይና ካልኣይ ማስረጃዎች ላይ ተንተርሶ እንደሚጻፍ መነሻ ጽሁፍ አቅራቢው ገልጸው፤ ሙያዊ አጻጻፍ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአገረ ጀርመንና በአገረ ፈረንሳይ መጀመሩን አንስተዋል። በአፍሪካ ታሪክ አጻጻፍ ግን ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ መምጣቱን አስታውሰዋል። በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ ታሪክ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ ዜና መዋዕላት መልክ መጀመሩን ጠቅሰዋል። የዜና መዋዕላቱ አፃፃፍ ወደ መንፈሳዊነት ቢያዘነብልም ዜና መዋዕላቱ ባይኖሩ የኢትዮጵያን ታሪክ መጻፍ እንደማይቻል ገልጸው እነዚህ ሰነዶች ታሪክን ለመጻፍ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት መጀመሩን፣ ሙያዊ/አካዳሚክ/ ታሪክ አጻጻፍን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍልና የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ምስርታ ጋር አስተሳስረውታል። በቀደማዊ አጼ ኃይለስላሴ መጨረሻ ዘመናትና በዘመነ ደርግ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት 'በኢትዮጵያ ታሪክ እውቀት ወርቃማ ዘመናት' መሆናቸውን ፕሮፌሰር ባህሩ ጠቅሰዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች እንዳሉት ገልጸው፤ የቋንቋ እውቀትን ጨምሮ የተመራማሪዎች ደረጃ ማሽቆልቆል፣ ተተኪ አለማፍራት፣ ምርምርና ስርፀት መቀዛቀዝና ያለመደራጀት ችግር በውስጣዊ ተግዳሮትነት ተነስተዋል። በሌላ በኩል ከዳግማዊ ምኒልክ እስክ ኢህአዴግ መንግስታዊ ጫና መኖር፣ ታሪክን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ መጠቀምና ታሪክን የማጠልሸት ተግባር ዋነኛ ተግዳሮቶች ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል። ለአብነትም ታሪክን እንደፖለቲካ መሳሪያ በመጠቀም ረገድ የኤርትራ ነጻነት ግንባሮችና ደጋፊዎቻቸው በኩል የኢትዮጵያ 100 ዓመት ታሪክ ፈጠራ፣ የኤርትራና ኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ሴራ ሲሆን በኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኞች በኩል ደግሞ ኢትዮጵያና ኦሮሞ እንደ ጎረቤት አገር የመቁጠር፤ የጋራ ታሪክ የለምና መሰል የተሳሳቱ ትርክቶችም መበራከታቸውን ይጠቀሳሉ። 'ኢትዮጵያ ነጻነቷን ያስጠበቀችው በኢምፔራሊስቶች ድጋፍ ነው፣ ታሪክን ፈረንጅ አይጽፍም' ሌላው ውጫዊና ከሙያዊ ከታሪክ አጻጻፍ መርህ ውጭ መሆኑን ተናግረዋል። ታሪክን ከማጠልሸት ረገድም ምሁራንና ፖለቲከኞች በሙያዊ ታሪክ አጻጻፍ ስልት ታርክ ከመጻፍ ይልቅ የታሪክ ፀሐፍትን ማጠልሸት ተግባራት ላይ መሰማራታቸውን አብራርተዋል። ፕሮፌሰሩ የወደፊት አቅጣጫዎችን ሲያስቀምጡም በቤተ መንግስትና በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የተቀመጡ መዛግብትን ማሰባሰብና ተደራሽነነታቸውን ማጠናከር፣ የንቁ አንባቢ ባህል መፍጠር፣ የሚያግባባ የጋራ ታሪክ መፍጠር፣ ታሪክን ከፖለቲካ ተገዥነት ማላቀቅ፣ ሐቅና ሚዛናዊ መርሆችን በመከተል መጓዝ ይጠይቃል ነው ያሉት። "የጋራ ታሪኮች ላይ መግባባት መፍጠር ይገባል፤ ታሪክ ትምህርት ቤት እንጂ እስር ቤት መሆን የለበትም" ብለዋል። "በዓለም ላይ በደምና በአጥንት እንጂ በሕዝበ ውሳኔ የተመሰረተ አገር የለም" ያሉት ፕሮፌሰር ባሕሩ፤ "በኢትዮጵያ መልካምም፣ መጥፎም ታሪካዊ ክስተቶችም መፈጠራቸውን ተናግረዋል። "በትናንት ታሪክ ማላዘን አይጠቅምም፤ ከዚያ ይልቅ የተሻለ ነገር ለመፍጠር ወደፊት መራመድ ይገባል" ብለዋል። "ምርጫውም አብሮ መኖር ወይም አብሮ መጥፋት ነውም" ብለዋል። በሌላ በኩል የታሪክ ዕውቀት የፖለቲካ ችግር እያስከተለ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ የትምህርት ስርዓቱና ተቋማቱ ለታሪክ ትምህርት ትኩረት ሊሰጡት፣ ለጥናትና ምርምር በጀት ሊመደብለትና ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ በመድረኩ ተጠቅሷል።