ቀጥታ፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የተካሄደው የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያለውጤት ተጠናቀቀ

ኢዜአ ጥር 1 /2012.. በአዲስ አበባ በታላቁ ህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ የተካሄደው የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያለውጤት ተጠናቀቀ። ላለፉት ሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ያተኮረው በግድቡ ውሃ አሞላል፣ አለቃቀቅና ሌሎች ተያያዥ የግድቡ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ነበር። አገራቱ በግድቡ የቴክኒክ ጉዳይ ላይ የሚያካሄዱት ድርድር ይህ 4ኛና የመጨረሻው እንደነበርም ተነግሯል። ውይይቱ ያለውጤት የተጠናቀቀው አጀንዳዎቹ ላይ በግብፅ በኩል በተንፀባረቀው አሉታዊ አስተሳሰብ ሳቢያ መሆኑን ኢትዮጵያ አስታውቃለች። የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ እንዳሉት የግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ ግብጽ ያቀረበችው አዲስ ሀሳብ ውይይቱ ያለውጤት እንዲጠናቀቅ ምክንያት ሆኗል። "ግብፅ የህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌትን አስመልክቶ የራሷን መንገድ የተመለከተ ሀሳብ ማቅረቧና በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአገሪቱ ልኡካን ቡድን አባላትም ሀሳቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ መጎትጎታቸው ስብሰባው ውጤት ላይ እንዳይደርስ አድርጎታል" ሲሉ ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት። ግብጽ ያቀረበችው ይህ አዲስ ሀሳብ ሲበዛ ፍትሃዊነት የራቀው መሆኑን የገለፁት ዶክተር ስለሺ ግብፅ ያቀረበችው ሀሳብ የግድቡ ውሃ ሙሌት ከ12 አስከ 21 ዓመታት የሚወስድ ነው ብለዋል። ይህም በኢትዮጵያ በኩል ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንደሌለው በመጠቆም። ቀደም ሲል የውሃ ሙሌቱ ከ4 እስከ 7 ዓመት ጊዜ ውስጥ ይከናወን ዘንድ ኢትዮጵያ ሀሳብ አቅርባለች። የህዳሴ ግድብ በተያዘለት የሰባት ዓመት የውሃ መሙላት የጊዜ ገደብ መሰረት በመጪው ሐምሌ ጀምሮ ወደ ሥራ እንደሚገባም ዶክተር ስለሺ ተናግረዋል። በተጨማሪም በአካባቢው ድርቅ ቢያጋጥም በግድቡ ውሃ አለቃቀቅ ዙሪያ ሦስቱ አገራት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ግብፅ ግን ከአሰዋን ግድብ ጋር መያያዝ ይኖርበታል የሚል ሀሳብ በድጋሚ ማንሳቷል ገልጸዋል። ሆኖም በውይይቱ ላይ "ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሀሳብ በድርቅ ወቅት የህዳሴው ግድብ 35 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ ወደታች ይለቃል፤ ግድቡ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰና የአሰዋን ግድብ ወደ መዝጊያው ከደረሰ ከተጠራቀመው  ተጨማሪ ውሃ በመልቀቅ ድርቁን መቋቋም ይቻላል"  የሚል ሀሳብ መንሸራሸሩንም አንስተዋል። በውይይቱ ላይ በግብጽ በኩል አሉታዊ አስተሳሰብ የተንፀባረቀ ቢሆንም የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ውይይቱን ያካሄደው በከፍተኛ የመተማመንና የትብብር መንፈስ መሆኑንም ዶክተር ስለሺ ገልፀዋል። በቀጣይም የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች የእስካሁኑን የሶስትዮሽ ስብሰባ ሂደት ሪፖርት ለሀገሮቻቸው መሪዎች ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃለ። የፊታችን ሰኞ ጥር 4 ቀን 2012 ዓም ወደዋሽንግተን በማምራት የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ በተገኙበት ቀጣይ ውይይት ያደርጋሉ። የሀገራቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጭምር በሚሳተፉበት በዚህ የዋሽንግተን ውይይት ላይ ባለፉት አራት ተከታታይ የሚኒስትሮች የቴክኒክ ስብሰባዎች ዙሪያ ገለፃ ይደረጋል። ሀገራቱ በዋሽንግተኑ ስብሰባቸው የድርድር ሂደቱን በመቋጨት ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሶስቱ ሀገራት በዋሺንግተን ዲሲ በደረሱት ስምምነት አማካኝነት እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ስምምነት ላይ ካልደረሱ ካርቱም ላይ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ የተፈረመው የመርሆዎች ስምምነት አንቀጽ 10 ተግባራዊ እንዲሆን ይደረጋል። የካርቱም የመርሆዎች ስምምነት 10 አንቀጾች የያዘ ሲሆን የመጨረሻው አንቀጽ 10፤ "ሶስቱ አገራት በመርሆዎች ስምምነቱ አተረጓጎምና ተግባራዊነት የተነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ወይም በድርድር ይፈታሉ፤ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን አደራዳሪ ሊጠይቁ ወይም ለአገራቸው ርዕሳነ ብሔሮችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሊያሳውቁ ይችላሉ" ይላል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም