በባሌ ዞን የአንበጣ መንጋን ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የመድኃኒት ርጭት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን የአንበጣ መንጋን ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የመድኃኒት ርጭት እየተካሄደ ነው
ኢዜአ ጥር 1/2012... በባሌ ዞን የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በአውሮፕላን የታገዘ የመከላከል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በጽህፈት ቤቱ የሰብል ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደሜ ሁንዴ ለኢዜአ እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው በተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች ተከስቷል፡፡ በዋናነት ሰዌና፣ መዳ ወላቡ፣ሀረና፣ጎሮ፣ጉራ ዳሞሌ፣ጊኒር፣እና ራይቱ ወረዳዎች ውስጥ በስፋት እንደሚገኝ በተደረጉ ቅኝቶች መረጋገጡን አመልክተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በሰው ኃይል ለመከላከል ጥረቱ ቢኖርም መንጋው ስፋት ያለው በመሆኑ ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ በአውሮፕላን የታገዘ የመድኃኒት ርጭቱ እየተካሄደ ይገኛል። በተለይ አሁን በመኽሩ የለማው ሰብል የሚሰበሰብበት ወቅት በመሆኑ የአንበጣው መንጋ እንቅስቃሴ ሰፍቶ በሚታይባቸው የተመረጡ ቦታዎች ላይ እስካሁን በሰው ኃይልና በአውሮፕላን 500 ሊትር መድኃኒት ርጭት መካሄዱን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡ ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት የመከላከል ስራ እያገዙ መሆኑን አስተባባሪ ጠቁመው ሳይስፋፋ ለመቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል። አቶ ኡስማን ጀማል በደሎ መና ወረዳ መልካ አማና ቀበሌ በመከላከሉ ስራ ከተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዱ ናቸው። በአካባቢያቸወ የተከሰተው የአንበጣውን መንጋ የተለያዩ ድምጾችን በማሰማት ለማባረር ጥረት እደረጉ መሆናቸውን በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል። አቶ ኡስማን እንዳሉት መንጋው በባህላዊ ዘዴ ብቻ በሚያደርጉት ጥረት በሚፈለገው ደረጃ መከላከል ባለመቻለቸው የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሰረት የሆነው የእንስሳት መኖ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። "አሁን በመኽሩ ወቅት ያለማነውን ሰብል የምንሰበስብበት ወቅት በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርሰብን ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል" ያሉት ደግሞ የጎሮ ወረዳ ነዋሪው አቶ አበራ ከተማ ናቸው፡፡ የአንበጣ መንጋው መከሰቱ የታወቀው ታህሳስ 13/2012 ዓ.ም ባሌን ከሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስነው ራይቱ ወረዳ ውስጥ እንደሆነ ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡ በባሌ ዞን በመኽሩ ወቅት በተለያየ ሰብል ከለማው 335ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 50 በመቶ መሰብሰቡን ከእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡