ቀጥታ፡

የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ

ኢዜአ፤ ጥር 1/2012 የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ። ሶዶ ላይ የአምናው የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ከጠዋቱ 3 ሰአት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በስምንት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ እስካሁን በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠመውም። በዘንድሮው የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበው አዲስ አበባ ፖሊስ በሊጉ ያደረጋቸውንም አራቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሁለቱ ክለቦች ካላቸው ወቅታዊ ብቃት አንጻር የእሁዱ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል። እሁድ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ባህርዳር ላይ ከጠዋቱ 3 ሰአት እስካሁን በሊጉ ያደረጋቸውን አራቱንም ጨዋታዎች የተሸነፈው ጣና ባህርዳር በሊጉ በስምንት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው መዳወላቡ ዩንቨርስቲ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 መከላከያ ከሊጉ መሪ ሙገር ሲሚንቶ ከረፋዱ 4 ሰአት ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጋር ይጫወታሉ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን በመጪው እሁድ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ ምክንያት የቀን ሽግሽግ ተደርጎባቸዋል። በዚሁ መሰረት ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ሊደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ሊደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች ጥር 5 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄዱ ይሆናል። በዚሁ መሰረት ሰኞ ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከጠዋቱ 3 ሰአት ፌደራል ፖሊስ ከከምባታ ዱራሜ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 ይጫወታሉ። ማክሰኞ ጥር 5 ቀን 2012 ዓ.ም ሶስት ጨዋታዎች በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን ከተማ ከቡታጅራ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ 3 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከመከላከያ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 ይጫወታሉ። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ነገ ቅዳሜና እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል። በዚሁ መሰረት በሴቶች ነገ ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2012 ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከየካ ክፍለ ከተማ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። በተከታዩ ቀን እሁድ ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ከጠዋቱ 3 ሰአት፤ ጅማ ላይ ጅማ ከተማ ከአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከረፋዱ 4 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በወንዶች ነገ ቅዳሜ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከየካ ክፍለ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰአት፤ በተከታዩ ቀን ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰዓት የሚጫወቱ ይሆናል። አዲሱ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ አጋዚ ውቅሮ በወንዶች በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ የማያደርግ በመሆኑ አራፊ ክለብ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም