ኢትዮጵያ በአየር ጸባይ ለውጥ የተጎዱ ዜጎቿን ህይወት የሚያሻሻል ድጋፍ ከአለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ አገኘች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአየር ጸባይ ለውጥ የተጎዱ ዜጎቿን ህይወት የሚያሻሻል ድጋፍ ከአለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ አገኘች
ኢዜአ ታህሳስ 30 / 2012 ኢትዮጵያ በአየር ጸባይ ለውጥ የተጎዱ ዜጎቿን ህይወት የሚያሻሻል ድጋፍ ከአለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ አግኝታለች። 305 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ይኸ ፕሮግራም በአየር ጸባይ ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቁና ከ 13 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል። ድጋፉ የአርሶ አደሮቹን ገቢና የገቢ ስብጥር ለማሳደግ፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆንና በአየር ጸባይ ለውጥ የተጎዳው አካባቢያቸው እንዲያገግም እንደሚያግዝም ተጠቅሷል። የድጋፍ ስምምነቱ የአለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ ፕሬዝዳንት ጊልበርት ኤፍ ሆንግቦ እና በተባበሩት መንግስታት የምግብና የግብርና ኤጀንሲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና ቋሚ መልዕክተኛ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ መካከል የተፈጸመ ሲሆን ጣሊያን ሮም ላይ ነው የተካሄደው። “በገጠር ለሚኖሩ ዜጎች የፋይናንስ ተደራሽነቱ በጣም አስፈላጊ ነው፤ በተለይም በአየር ጸባይ ለውጥ ገቢያቸው የቀነሰባቸው ሰዎች ንግዳቸውን እንዲያስፋፉ እና በግብርናና በግብርና ማቀነባበር ዘርፍ በመታገዝ አዲስ አይነት የአኗኗር ዘይቤ እንዲላመዱ ያደርጋቸዋል" በማለት የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አገራዊ ተጠሪ ኡላክ ዲሚራግ ናቸው። “ፕሮግራሙ በእጅጉ ወደ ኋላ በቀሩ አካባቢዎች ለሚኖሩ ነዋሪዎች የገንዘብ ቁሶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ የድህነት ምጣኔውን እንዲቀንሱና በኑሮአቸው የሚገጥማቸውን የአደጋ ስጋት ተቋቁመው እንዲያልፉ የሚያሰቸል ነውም" ሲሉ ተጠሪው ገልጸዋል። ፕሮግራሙ ከዚህ ቀደም ከተተገበሩት ሁለት ምዕራፍ ተግባራት በተቀሰመው ልምድ በመታገዝ የገጠር ፋይናንስ አቅርቦቱን እጅግ ለተጎዱ አነስተኛ አምራች አርሶ አደሮች በተለይም ለሴቶችና ወጣቶች ይቀርባል። ከዚህ ባለፈ የገጠር የፋይናንስ ተቋማትን አቅም በማሳደግ ለገጠሩ ህብረተሰብ የሚያቀርቡትን የፋይናንስ ምርትና አገልግሎት እንዲያሳድጉም ያግዛቸዋል። በተጨማሪም እነዚህን ምርቶች በተመለከተም ለገጠር የቁጠባና ብድር ተቋማት እና አነስተኛ የብድር አገልግሎት ተቋማት ስልጠና በመስጠት እንዲረከቧቸው ለማድረግ ያስችላልም ተብሏል። ፕሮግራሙ በአየር ጸባይ ለውጥ በጣም የተጎዱና ለምግብ ዋስትና እጥረት የተጋለጡ አካባቢዎችን በመለየትና የአመጋገብ ግንዛቤን በዘመቻ መልክ በማሳደግ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። ከድጋፉ 35 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላሩ ከአለም አቀፉ የምግብና የግብርና ልማት በድጋፍ የተገኘ ሲሆን 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ በብድር ተገኝቷል። አለም አቀፍ የልማት አጋሮችና አገር አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ 51 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ያወጣ ሲሆን ተጠቃሚዎቹም የራሳቸውን ድርሻ ያዋጣሉ። አለም አቀፉ የምግብና የግብርና ልማት ተቋም አ.አ.አ ከ 1980 አንስቶ በ 20 የገጠር ልማት ፕሮግራምና ፕሮጀክት 795 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ከ 12 ሚሊዮን የሚልቁ የገጠር ነዋሪዎቸን ተጠቃሚ ማድረጉ በዘገባው ተጠቅሷል።