በከለላ ከተማ የኤሌክትሪክ መቋረጥ ችግር መፍትሄ እንዲሰጣቸው ነዋሪዎች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
በከለላ ከተማ የኤሌክትሪክ መቋረጥ ችግር መፍትሄ እንዲሰጣቸው ነዋሪዎች ጠየቁ
ኢዜአ ታህሳስ 30 / 2012 በኤሌክትሪክ መቋረጥ እያጋጠማቸው ላለው ችግር አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው በደቡብ ወሎ ዞን ከለላ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ። ችግሩን ለመፍታት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ነባር መስመሮችን በአዲስ የመለወጥ ስራ መጀመሩን በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ዲስትሪክት አስታውቋል።
በከላላ ከተማ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ አቶ አህመድ ሰይድ ለኢዜአ እንዳሉት በኤሌክትሪክ መቋረጥ ያቋቋሙት የእህል ወፍጮ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መሰጠት አልቻለም።
"ወፍጮው በወር ውስጥ ለ15 ቀን እንኳ እያገለገለ አይደለም”ያሉት አቶ ሰይድ ባልሰሩበት ሁኔታ የመንግስት ግብርና የሰራተኛ ደመወዝ መክፈል እየተቸገሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለቀናት ተቋርጦ ቆይቶ የሚመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል እያስከተለ ያለው የ"ዲናሞ " መቃጠል ለአላስፈላጊ ወጭ እንየዳረጋቸው መሆኑን በማመልከት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
“በተደጋጋሚ የሚያጋጥም የኤሌክትሪክ መቋረጥ በስራየ ላይ ጫና ፈጥሮብኛል” ያሉት ደግሞ በከተማው የቀበሌ አንድ ነዋሪና የምግብ ቤት ባለቤት አቶ አወል ያሲን ናቸው።
ለምግብ ማብሰያነት የኤሌክትሪክ እቃዎችን መጠቀም ባለመቻላቸው ለከሰልና እንጨት ማገዶ ግዥ በወር ከ800 ብር በላይ ወጭ እንዲያወጡ መገደዳቸውን አመልክተዋል።
የሚመለከተው አካል ለችግራቸው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብቱ አበበ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ችግሩ ከለላን ጨምሮ በደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች እንዳለ ተናግረዋል።
ስራ አስኪያጁ እንዳሉት ችግሩን ለመፍታት በ200 ሚሊዮን ብር በጀት የአዲስ መስመር ዝርጋታ ተጀምሯል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ነባር ምሶሶና የመስመር ሽቦ በአዲስ የመተካት ስራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል ።