ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቆላ ስንዴን በመስኖ በማልማት ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረብ ትችላለች - የግብርና ተመራማሪዎች

ኢዜአ፤ታህሳስ 30/2012 ኢትዮጵያ የቆላ ስንዴን በመስኖ በማልማት ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችላት እምቅ አቅም እንዳላት የግብርና ተመራማሪዎች ገለጹ። የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎት 65 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል፤ ከዚህ ውስጥ 48 ሚሊዮን ኩንታሉ በአገር ውስጥ ምርት ሲሸፈን ቀሪው ከውጭ እንዲገባ ይደረጋል። አገሪቷ ቀሪውን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማሟላት ከ600-700 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ታወጣለች። ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 60 በመቶ የሚሆነው ቆላማና አብዛኞቹ ወንዞች የሚፈሱባት በመሆኑ የቆላ ስንዴን በቀላሉ በመስኖ ማልማት ትችላለች። የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ መርሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ቆላማ ስፍራ ከደጋው በሚነሱ ወንዞች ደለል ስለሚሞላ መሬቱ ለም ነው።

በዚህም የከርሰ ምድር ውሃና የወንዞችን ተፋሰስ በመጠቀም የቆላ ስንዴ በቀላሉ ማልማት የሚቻልበት እድል አለ ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቆላ ስንዴ አስተባባሪ ዶክተር ዳንኤል ሙለታ በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ያለው ከ400 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በመስኖ የቆላ ስንዴ ቢለማ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ማስቀረት ይቻላል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች በወንዞች ተፋሰስና በከርሰ ምድር ውሃ የከበሩ በመሆናቸው በቀላሉ ስንዴ ማምረት እንደሚቻል አሁን በሙከራ ደረጃ ያለው የቆላ ስንዴ ምርት ማሳያ ነው ብለዋል።

በወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የዕፅዋት አዳቃይ ተመራማሪ አቶ ደስታ ገብሬ በአዋሽ ተፋሰስ ስር ብቻ በመስኖ መልማት የሚችል ከ206 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዳለ ይናገራሉ።

የአዋሽ ወንዝ ለግብርና ምርት እድገት አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ ያለምንም ማዳበሪያ በቀላሉ ስንዴ ማምረት እንደሚያስችል በመጥቀስ።

ዶክተር ዳንኤል ሙለታ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና አቶ ኡስማን ከድር ከአዳሚ ቱሉ ግብርና ምርምር ማዕከል እንዳሉት የተጀመረው የቆላ ስንዴን በመስኖ የማልማት መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆን ኅብረተሰቡን ማንቃትና አሰራረ መዘርጋት ይገባል።

 

የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የቆላ ስንዴ ምርትን ውጤታማ ለማድረግ ለቆላ ስነ ምህዳር ተስማሚ ዝርያዎችን ማውጣትና ማባዛት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዚህም በሚቀጥለው ዓመት ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ ዝርያ ለአምራቶች ለማቅረብ በ4 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ ዘር እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከአራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ መልማት የሚችል ቢሆንም አሁን እየለማ ያለው ከሁለት በመቶ አይበልጥም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም