ቀጥታ፡

የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ

ኢዜአ፤ታህሳስ 30/2012  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 5ኛ አመት የስራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ስብሰባ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ በሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በሚል አፅድቆታል።

ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ፣ በሁለት ተቃውሞና በአራት ድምፀ ተአቅቦ ነው አዋጁን ያፀደቀው።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከቀረበ በኋላ የምክር ቤቱ አባላት አስተያየትና ጥያቄ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

የሀገርና የህዝብን ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ግለሰቦችና ድርጅቶች ሀብትና ንብረታቸውን ለመጠበቅ የሚይዟቸውን መሳሪያዎች በህግና በስርዓት ማስተዳደር ከአዋጁ ዓላማዎች ናቸው።

እስካሁን በሀገር ደረጃ ወጥ የሆነ የጦር መሳሪያ አያያዝና ቁጥጥር ለማደረግ የሚያስችል ህግ ባለመኖሩም የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላትና ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመቆጣጠር የጦር መሳሪያን በመንግስት ተቋም ብቻ ለማስተዳደርም ነው አዋጁ ያስፈለገው።

በረቂቅ አዋጁ ላይ ጉዳት አድራሽ እቃ ተብለው የተጠቀሱት ገጀራ፣ ሜንጫ፣ ጦርና ቀስት የማህበረሰቡ የእለት ተእለት መገልገያና የባህል መገለጫ በመሆናቸው መካተታቸው ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት በአባላቱ ተነስቷል።

እንዲሁም  የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ፍቃድ የተሰጠው ሰው ፍቃድ ከተሰጠው ክልል ውጪ ባሉ የክልልና ትላልቅ ከተሞች የጦር መሳሪያውን ለህዝብ በሚታይ መልኩ ታጥቆ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑም በአዋጁ አንቀፅ 5/1 "ሸ" ተገልጿል።

የጦር መሳሪያ ውርስን በተመለከተም ውርሱ እናቶችንና ሴቶችን ቢያካትትም ሌሎች የቤተሰብ አባላትን ማካተት እንደሚኖርበትም አባላቱ አንስተዋል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ጉዳት አድራሽ እቃዎችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ እቃዎቹ ለልማትና ለእርሻ ስራ ሲተገበሩ ሳይሆን ሰውን ለማጥቃት መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ ነው አዋጁ የሚደነግገው ብለዋል።

አዋጁ የኀብረተሰቡን ሰላምና ፀጥታ ማስጠበቅ ዋና አላማው መሆኑን ጠቅሰው ጉዳት አድራሽ መሳሪያዎችም በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሰው ህይወትን ለማጥፋት መጠቀሚያ ሲሆኑ መስተዋሉንና ህጉም ይህን ለመከላከል የሚያስችል እንደሆነ አንስተዋል።

የጦር መሳሪያ ሰዎች ንብረታቸውንና የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት የሚጠብቁበት በመሆኑም ፍቃድ ከተሰጠበት ክልል ውጪ ወደሌላ አካባቢ እንዳይጓዝ መገለፁንም አንስተዋል።

ውርስን በተመለከተም ማሻሻያ መደረጉንና በውርስ ህጉ መሰረት እንደሚሰራና ማንኛውም ህጉ የሚፈቅድለት ሰው መውረስ እንደሚችል አስረድተዋል ሰብሳቢው።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው አዋጁን ከማፅደቅ በተጨማሪ የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅንና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም