ቀጥታ፡

ማላዊ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች

ኢዜአ፤ታህሳስ 30/2012 ማላዊ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጻለች።

የማላዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንሲስ ካሳሊያ መቀመጫቸውን ናይሮቢ ያደረጉትን በኬንያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለምን በማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ ትላንት አነጋግረዋል፡፡

አምባሳደሩ በማላዊ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለማቅረብ መሄዳቸው በኢትዮጵያና በማላዊ መካከል የቆየውን ወዳጅነት የሚያጠናክር በመሆኑ በቀጣይ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

“አዲስ አበባ የሁሉም አፍሪካዊ ቤት ናት” ያሉት ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በቀጠናው ሰላም እንዲመጣ እያደረጉ ያሉትን ጥረት እንደሚያደንቁ ተናግረዋል።

መቀመጫቸውን ናይሮቢ በማድረግ ማላዊን፤ ሲሸልስ እና ኮሞሮስን የሚሸፍኑት አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው ወዳጅነቱ በንግድ፣ በአቪዬሽን እና በግብርና መስኮች እንዲጠናከር የኢትዮጵያም ጽኑ ፍላጎት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶች በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታን ሁለቱም ሀገሮች ማመቻቸት ይግባቸዋልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ሰባት ቀን ወደ ማላዊ እንደሚበርና ከማላዊ አየር መንገድ ጋር በስራቲጂካዊ አጋርነት መስራታቸው የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ እንደሚያስተሳስር በመግለጽ፤ ህግወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከል ላይ መስራት እንደሚፈልጉም አምባሰደሩ ገልጸዋል።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለማላዊ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፒተር ሙንታሪካ እንደሚያቀርቡ ከውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም