ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለመጀመር ዝግጅት ተደረገ

ታህሳስ 30/2012   በአማራ ክልል ከጥር 4/2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ በህዝባዊ ንቅናቄ ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። ስራው የሚከናወነው  በክልሉ  154 ወረዳዎች ውስጥ በተመረጡ ሰባት ሺህ 600 ተፋሰሶች ነው።

የቢሮው የተፈጥሮ ሃብል ልማት ዘርፍ ቢሮ  ምክትል  ኃላፊ አቶ ማርቆስ ወንዴ  እንደገለጹት በተፋሰሶቹ ውስጥ ከሚከናወኑት መካከል የማሳና የጋራ ላይ ዕርከን፣ የክትር፣ የውሃ ማፋሰሻ ቦዮች ስራና  የደን ልማት ይገኙበታል።

በዚህም  260 ሺህ ሄክታር መሬት  በአዲስ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ እንዲሁም 400 ሺህ ሄክታር ደግሞ መልሶ የማጠናከር ስራ  ይሸፈናል።

ስራው ለ20 የስራ ቀናት የሚቆይ ነው።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎቹ ግድቦችና ውሃ አዘል መሬቶች በደለል እንዳይሞሉ በራስ ዳሽን፣ አቡነ ዮሴፍ፣ ጮቄ፣ ጉናና ሌሎች ተራራማ ቦታዎች ከተፋሰስ ልማት ጋር በማቀናጀት እንደሚሰራም አመልክተዋል።

ስራውን ለማከናወን የሚያስችል የሰው ኃይል፣ የነፍስ ወከፍ የስራ መሳሪያዎች መለየት ፣ ለቀያሽ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት ቢሮው ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

በልማት ስራው ከ4 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች  እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

ከአርሶ አደሩ፣ ባለሙያውና በየደረጃው ካለው አመራር ጋር በተደረሰው የጋራ መግባባትም የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች ዘላቂነ በሚያረጋግጥ አግባብ እንዲከናወን  የቢሮው  ምክትል  ኃላፊ  አስረድተዋል።"በየዓመቱ የሚሰራው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የአፈር ለምነት እንዲጨምር፣ የተራቆተ መሬት መልሶ እንዲያገግም ከማድረግ ባለፈ የከርሰ ምድር የውሃ ሃብትን በማጎልበት ለመስኖ ልማት ስራው አስተዋፅኦ እያደረገ ነው "ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በተከናወነው የተፈጥሮ ሃብል ልማትና ጥበቃ ስራ ከ6 ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ የተጎዳ መሬት ማገገሙን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም