የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ ስልጠና ከጥር 1 ጀምሮ በአዲስ አበባ ይሰጣል - ኢዜአ አማርኛ
የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ ስልጠና ከጥር 1 ጀምሮ በአዲስ አበባ ይሰጣል
ኢዜአ ታህሳስ 29/2012 የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ ስልጠና ከጥር 1 እስከ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ይሰጣል። ስልጠናው የሚሰጠው ከደቡብ ኮሪያ የወርልድ ቴኳንዶ ቹንግ ዶ ኳን ፌዴሬሽን አሰልጣኞች በመጡት ግራንድ ማስተር ሺን ቹንግ ዶ ኳን እና ኩኪዋን አማካኝነት ነው። በአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽንና ኢትዮ-ፋይት ናይት ትብብር በሚሰጠው በዚህ ስልጠና ከ100 እስከ 120 የሚሆኑ አሰልጣኞች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በስልጠናው ላይ የሚሳተፉት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ዳን ያላቸው አሰልጣኞች ሲሆኑ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኬንያና ታንዛንያ የሚመጡ አሰልጣኞችም ይሳተፋሉ ተብሏል። የኢትዮ-ፋይት ናይት መስራችና ሃላፊ ማስተር ዳግማዊ ወርቅነህ ለኢዜአ እንደገለጹት በንድፈ ሀሳብና በተግባር የሚሰጠው በዚህ ስልጠና ራስን መከላከልና ሌሎች መሰረታዊ የወርልድ ቴኳንዶ ቴክኒኮች ይካተታሉ። ስልጠናው በኢትዮጵያ የሚገኙ የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች አቅማቸውንና ያሉበትን ደረጃ የሚያዩበት እንደሆነም ተናግረዋል። የወርልድ ቴኳንዶ ቹንግ ዶ ኳን ፌዴሬሽን በአፍሪካ ይሄን አይነት ስልጠና ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም አመልክተዋል። ከፌዴሬሽኑ የመጡት ግራንድ ማስተሮች ዘጠነኛ ዳን እንዳላቸውና ስምንተኛ ዳን ያላቸው አየርላንዳዊው ሼመስ ኦኔል ከሁለቱ አሰልጣኞች ጋር ስልጠናውን እንደሚሰጡም ነው ማስተር ዳግማዊ ያስረዱት። ስልጠናው አሰልጣኞች የሙያ አቅማቸውን እንዲያሻሽሉ የተዘጋጀ እንጂ የዳን ደረጃ ማሻሻያ ፈተና እንደሌለውም አክለዋል። በቀጣይም ከአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በሚገኝ ፈቃድ የዚህን መሰሉን የአሰልጣኞችና የተወዳዳሪዎች ስልጠናና ውድድር ለማዘጋጀት እቅድ እንዳለም አክለዋል። የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሃይሉ ጉተታ በበኩላቸው ስልጠናው እንዲዘጋጅ የተደረገው የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች ባቀረቡት ፕሮፖዛል አማካኝነት ነው ብለዋል። አሰልጣኞቹ ያቀረቡት ሀሳብ ለስፖርቱ እድገት ያላው ፋይዳ ታይቶ በአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን እና በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን እውቅና እንደተሰጠውም ገልጸዋል። በቀጣይ ጥር 2012 ዓ.ም አጋማሽም ለተወዳዳሪዎች የሚዘጋጅ ስልጠና እንደሚኖርም ጠቁመዋል። ፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቀጣይ የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞችና ተወዳዳሪዎች አቅማቸውን የሚያጎለብቱ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል። የወርልድ ቴኳንዶ አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ ስልጠና በኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽንም እውቅና እንዳለው ለማወቅ ተችሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የወርልድ ቴኳንዶ የመጨረሻው የዳን ደረጃ ዘጠነኛ ዳን ነው። የኮሪያ የባህል ስፖርት በሚል የሚታወቀው ወርልድ ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር ጥበባዊ ስልቶችን ያካተተ ክንዋኔ ሲሆን አእምሮና ሰውነት ማሰልጠንን ጨምሮ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝ የስፖርት ዓይነት እንደሆነም የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን ስፖርቱ ከአትሌቲክስ በመቀጠል በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ውጤት በማስገኘት አገሪቷን በማስጠራት ላይ ይገኛል።