ቀጥታ፡

ለውጭ ገበያ በሚቀርበውና በከፊል ያለቀለት ቆዳ ላይ ተጥሎ የነበረው ቀረጥ ሙሉ ለመሉ ተነሳ

ኢዜአ ታህሳስ  29/2012   ለውጭ ገበያ በሚቀርበውና በከፊል ያለቀለት ቆዳ ላይ ተጥሎ የነበረው ቀረጥ ሙሉ ለመሉ መነሳቱን የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። በቆዳ ዘርፉ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን አስመልክቶ ሚኒስቴሩ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረኢየሱስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በከፊል ያለቀለት ቆዳ ላይ ተጥሎ የነበረው ቀረጥ ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ የሚያስችለው መመሪያ ከታህሳስ 27 ቀነ 2012 ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል። የቆዳ ዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመለየት ጥናት መከናወኑንና በጥናቱ ግኝቶች ላይም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶች መደረጉን ገልጸዋል። በአገሪቷ የጥሬ ቆዳ ፍላጎት በአሳሳቢ ሁኔታ መቀነሱንና ቆዳዎች ጥቅም ላይ ሳይውሉ እየተወገዱ መሆኑም የጥናቱ ግኝቶች ካመላከቱት ችግሮች አንዱ ነው። ለውጭ ገበያ የሚቀርበውና በከፊል ያለቀለት ቆዳ ላይ ተጥሎ የነበረው ቀረጥ ማንሳት እንደሚያስፈልግ በጥናቱ የውሳኔ ሀሳብ ላይ በቀረበው መሰረትም ማሻሻያው ተግባራዊ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። በዘርፉ ላይ የተደረገው ማሻሻያም በከፊል ያለቀለት ቆዳ የኤክስፖርት አፈጻጻሙን በማሻሻል አገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ማሳደግና የስራ እድል ማስፋት መሆኑም ገልጸዋል። ከፋይናንስ፣ ከውጭ ምንዛሬ እጥረትና ሌሎች በዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችንም ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል። አቶ ተካ እንደገለጹት በዘርፉ የተሰማሩ ባለ ሀብቶች በሂደት ያለቀለት ቆዳ እንዲልኩ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መመሪያም እየተዘጋጀ ነው። የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንደስትሪዎች ማህበር የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ያሬድ አለማየሁ በበኩላቸው በከፊል ያለቀለት ቆዳ ላይ 150 በመቶ ቀረጥ  በመጣሉ ሳቢያ በዘርፉ ከተሰማሩ 17 ፋብሪካዎች 6 መዘጋታቸውን ገልጸዋል። ስራ ላይ የቆዩት ፋብሪካዎችም ከማምረት አቅማቸው 50 በመቶ በማይበልጥ አቅም ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል። በዘርፉ የነበረው  ከፍተኛ ግብር መነሳቱ ዘርፉን የሚያበረታታና መንግስትና የግሉ ዘርፍ በቅርበት በመስራታቸው የተገኘ ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ አባተ ቀደም ሲል በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ቆዳ ተፈላጊና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያስገኝ እንደነበር አንስተዋል። ሆኖም በከፊል ያለቀለት ቆዳ ላይ በተጣለው ቀረጥ  ሳቢያ የውጭ ንግድ እንቅስቃሴውን እጅግ የደከመና ህገ ወጥ ንግድ እንዲስፋፋ ያደረገ ነበር ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የነበረውን ከፍተኛ ቀረጥ በማንሳት መንግስት ትልቅ እርምጃ መውሰዱን እንደ በጎ በማንሳት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም