ለኢንዱስትሪው ጥሬ ግብአት ማቅረብ ያልተቻለው በቂ ምርት እየቀረበ ባለመሆኑ ነው - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለኢንዱስትሪው ጥሬ ግብአት ማቅረብ ያልተቻለው በቂ ምርት እየቀረበ ባለመሆኑ ነው - ግብርና ሚኒስቴር
ኢዜአ፤ታህሳስ 29/2012 ለኢንዱስትሪው ጥሬ ግብአት በሚፈለገው መጠን ማቅረብ ያልተቻለው በየጊዜው እየጨመረ ያለውን የገበያ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ የሚያሟላ ምርት ማምረት ባለመቻሉ እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። በአገር አቀፍ ደረጃ ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርበውን ጥሬ ግብዓት ጨምሮ የሌሎች ሰብሎችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።
በኢትዮጵያ አገራዊ የምርት መጠን እድገት ባለፉት አምስት ዓመታት ከአምስት እስከ ስምንት በመቶ እያደገ መምጣቱንና ይሄም ለኢንዱስትሪው የሚቀርበውን ጥሬ ግብአት ያካተተ እንደሆነም ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ብቅል፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ተልባ፣ ኦቾሎኒና ኑግ ደግሞ ለኢንዱስትሪው ከሚቀርቡ ጥሬ ምርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ለኢንዱስትሪው የሚቀርቡ ጥሬ ግብአቶችም የሚቀርቡት በአነስተኛ አርሶ አደሮች ሲሆን ኢንዱስትሪው ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልገውን ክፍያ በመፈጸም ምርቱን የሚወስድበት ስርአትም ተዘርግቷል።
አገሪቷ ካላት ተስማሚ አየር ንብረትና መልክዓ ምድራዊ ምቾት አንጻር ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልገውን ጥሬ ግብአት ማቅረብ የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳለም ይነገራል።
ያም ቢሆን አሁንም ለኢንዱስትሪው የሚቀርበው ጥሬ ግብአት በአብዛኛው የሚገባው ከውጭ አገር እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ ይገልጻሉ።
ይሄም የሆነበት ምክንያት የምርት መጠን አሁን እየጨመረ በመጣው የገበያ ፍላጎት አኳያ በበቂ ሁኔታ እየቀረበ ባለመሆኑን በመግለጽ በዚህ ረገድም ስንዴን እንደማሳያነት አንስተዋል።
የምርታማነት መጠኑ በሚፈለገው ደረጃ ያላደገው አርሶ አደሩ አሁንም ድረስ ምርጥ ዘርን የመጠቀም ሁኔታ ዝቅተኛ መሆኑ በዋና ምክንያትነት የሚነሳ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
ምርጥ ዘር የሚጠቀመው የአርሶ አደሮች ቁጥር ከ15 በመቶ የማይበልጥ መሆኑን በማሳያነት በማውሳት።
ምርታማነትንም ለማሳደግ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሳደግና አርሶ አደሩ አዋጪ የሆኑ የሰብል ምርቶች ላይ እንዲሰማራ ሰትራቴጂካዊ ምርቶችን በክላስተር የሚያመርትበት የአሰራር ስርአት መፈጠሩን አመልክተዋል።
ከዚህም ባለፈ አሲዳማ አፈሮችን በማከም አርሶ አደሩ እንዲጠቀምባቸው እንዲሁም ኮትቻ አፈርን ለምርት በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነውም ብለዋል።
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አማካኝነት በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ እንደሆነም ይታወቃል።
በዚህም ረገድ ግብርናው ኢንዱስትሪውን ከመደገፍ አኳያ ሚኒስቴሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚፈልጉትን የሰብል ምርቶች የመለየትና አርሶ አደሮችን ጥሬ ግብአት እንዲያቀርቡ በተለዩት ሰብሎች በክላስተር የማደራጀት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በአገሪቷ ያሉት የዘይት ፋብሪካዎች በአሁኑ ሰአት ማምረት ከሚገባቸው አቅም በታች እያመረቱ እንደሚገኙና ለዚህም እንደ ችግር የሚያነሱት የጥሬ ግብአት በበቂ ሁኔታ አለማግኘት መሆኑም ይታወቃል።
እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ ለዘይት ምርት ጥሬ ግብአት በሚፈለገው ደረጃ እየቀረበ ያልሆነው በቅባት ሰብሎች ላይ ያለው የምርጥ ዘር አጠቃቀም በጣም ዝቅተኛ መሆኑና አርሶ አደሮች ለቅባት እህሎች የሚሰጣቸውን ዘር ለሌሎች ሰብሎች እየተጠቀሙበት በመሆናቸው ነው።
ለቅባት እህሎች የሚያስፈልገውን ዘር ፋብሪካዎች ብቻቸውን ማቅረብ እንደማይችሉና መንግስት ድጎማ ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
አቶ ኢሳያስ አክለውም ያሉትን ችግሮች በመፍታት ለዘይት ፋብሪካዎች የሚቀርበውን ጥሬ ግብአት በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል ፕሮግራም በቀጣይ የምርት ዘመን ሊጀመር እንደሚችልም ጠቅሰዋል።
በግብርናው መስክ በዋነኛነት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልገውን ጥሬ ግብአት በአገር ውስጥ ምርት መሸፈን እንደሆነና በዚህ ረገድም ሚኒስቴሩ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪዎችም የጥሬ ግብአት አቅርቦት እንዲያድግ ለአርሶ አደሩ የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግና ከአርሶ አደሩ ጋር ተቀራርቦ በመስራት የበኩላቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው ብለዋል።
በግብርናና በኢንዱስትሪው መካከል ባለው የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላት የጥሬ ግብአቱ ለኢንዱስትሪዎቹ በሚፈለገው ፍጥነት እንዲደርሱና ግብአቶቹ ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
ግብርና እና ንግድና ኢንዱስትሪው በቅንጅት በመስራት አገሪቷ በመስኩ ያላትን ችግር ለመፍታት ምን እየሰሩ እንደሆነ ለጠየቅናቸው ጥያቄዎች በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይረክቶሬት ለጊዜው ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም።