የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ አንዲመዘገብ የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ አንዲመዘገብ የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት ተጠናቋል

ኢዜአ፤ታህሳስ 29/2012 የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ አንዲመዘገብ የማስመረጫ ሰነድ ዝግጅት ተጠናቆ በመጪው መጋቢት እንደሚላክ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ የልጃገረዶች ጨዋታ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል የአደባባይ ክብረ በዓል በተለያዩ ባህላዊ ልብሶች በደመቁ ሴቶች ትውፊቱን ጠብቆ ለዘመናት ሲከበር ቆይቷል።
በአሉ በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ እንዳለው የታሪክ ድርሳናትና የቤተ-ክርስትያኒቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ።
በዓሉ ልጃገረዶች በባህላዊ አልባሳት አምረውና ተውበው ባህላዊ ዜማዎችን በጎዳና ላይ የሚያቀርቡበትና በውዝዋዜ የታጀበ ውብ ክብረ በዓል ነው።
ይህም በተለይ በትግራይና በአማራ ክልሎች ላይ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ባሉት ቀናት በተለያዩ ትዕይንቶች ደምቆ ይከበራል።
በአማራ ክልል ዋግህምራና በሰቆጣ አካባቢዎች "ሻደይ"፣ በላስታ ላሊበላና ጎንደር "አሸንድዬ" እንዲሁም በራያ ቆቦ ደግሞ "ሶለል" በዓል ተብሎ ይጠራል።
በትግራይ ክልል እንደርታና ተምቤን "አሸንዳ"፤ በአክሱም "አይኒዋሪ" እንዲሁም በአዲግራት አካባቢዎች ደግሞ "ማርያ" ጨዋታ ይሰኛል።
በዓሉ የክረምት መገባደድና የአዲስ ዓመት አዲስ ብስራት ዋዜማ የሚበሰርበት እንዲሁም ልምላሜ የሚታይበት ተደርጎም ይቆጠራል።
በዚህም ህጻናትና ወጣት ሴቶች እንዲሁም እናቶች በአደባባይ በመውጣት እለቱን እንደ ነጻነታቸው ቀን በመቁጠር "አሸንድዬ" የተባለውን ቄጠማ በወገባቸው ታጥቀው ከበሮ እየመቱ ከንጋት እስከ ምሽት ድረስ በጨዋታ ያሳልፉታል።
በዓሉ በተለይም ሴቶች ካለባቸው ድርብ ማህበራዊ ጫና ተላቀው በሙሉ ነጻነት ቀኑን ሙሉ ሲደሰቱበት የሚውሉበትም ነው።
በመሆኑም ይህን የጋራ እሴት የሆነው የልጃገረዶችና ሴቶች ባህላዊ ጨዋታን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የባህል ተመራማሪ አቶ ገዛኸኝ ግርማ የአሸንዳ፣ ሻደይና አሸንድዬ የልጃገረዶች በዓልን በዩኔስኮ እንዲመዘገብ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓትም በአሉ በማይዳሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ የማስመረጫ ሰነድና አስፈላጊ ጥናቶች ዝግጅት ተጠናቆ በመጪው መጋቢት እንደሚላክ ገልጸዋል።
ይህም በመንግስታቱ ድርጅት የማይዳሰስ ቅርስነት እንደሚመዘገብ የሚወሰን ከሆነ የኢትዮጵያ አምስተኛው የማይዳሰስ የአለም የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ይሆናል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እንደገና ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህል ሃብትና አቅም አንጻር በቱሪዝሙ የሚፈለገውን ያህል እየተጠቀመች እንዳልሆነ ያብራራሉ።
በዚህም ገና ብዙ የአለም ህዝብ ሊያውቃቸው የሚገቡና የቱሪዝም ሃብት ሊሆኑ የሚችሉ ቅርሶች እንዳሏትም ይገልጻሉ።
ይህንንም ለማጠናከር አገሪቷ ከዚህ ቀደም በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በተጨማሪ ሌሎችንም ቅርሶቿንና ሃብቶቿን ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም 8 የሚሆኑ ታላላቅ ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች በዩኔስኮ ጊዜያዊ መዝገብ ላይ ሰፍረው እንሚገኙ ጠቁመዋል።
እነዚህም የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ የድሬ ሼክ ሁሴን ኃይማኖታዊና ባህላዊ ስፍራ፣ የሆልቃ ሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የጌዲዮ ባህላዊ የመሬት አቀማመጥ፣ በልታ፣ የትግራይ መልክአ ምድር እንዲሁም የመልካ ቁንጥሬ እና የባችልት የስነ-ቁፋሮ ስፍራ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህን በጊዜያዊነት በዩኔስኮ ተመዝግበው የሚገኙትን ጨምሮ ሌሎች ጥንታዊ ስልጣኔና በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በአል በዩኔስኮ መመዝገብ አገሪቷ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ከማሳደጉም ባሻገር የአማራና የትግራይ ክልሎችን ህዝቦች ይበልጥ የሚያቀራርብና የሚያስተሳስር እንደሚሆንም ይታመናል።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው በአላት መካከል የመስቀል ደመራ፣ የጥምቀት፣ ፍቼ ጨምበላላና የገዳ ስርዓት ናቸው።