ቀጥታ፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚመክረው የሶስቱ አገሮች የሚኒስትሮች ቴክኒካል ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀምሯል

ኢዜአ፤ታህሳስ 29/2012 በኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው የሶስቱ አገሮች የውሃ ሚኒስትሮች ቴክኒካል ኮሚቴ የመጨረሻ ዙር ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የኮሚቴው ስብሰባ በግድቡ የውሃ አሞላል፣ አመራርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ታውቋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚዘልቀው ስብሰባ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች ከተመራው ኮሚቴ በተጨማሪ የአሜሪካና የዓለም ባንክ ተወካዮችም ተገኝተዋል።

የሶስቱ አገራት ሚኒስትሮች በውይይቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ድርድሩ ፍሬያማ ውጤት እንደሚያመጣ  ተስፋና ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር አንስቶ በግልጽ መርህ መመራቷን፣ ግድቡ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርስ የሚያረጋግጡ ከ150 በላይ ሰነዶችን ለሁለቱ አገራት ልካለች።

ላለፉት ዓመታት በርካታ የሶሰትዮሸ ድርድሮች ሲደረጉ ቆይተው ጉዳዩ አሁን ላይ በውሃ አሞላልና አመራር ደረጃ ላይ መድረሱን አውስተዋል። "ይህ ስብሰባ ድህነትን ለማስወገድ ታሪካዊ ዕድል ሰጥቶታል " ብለዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የውሃ ሃይል ማመንጫ ግድብ ለማህበረ-ኢኮኖሚ ልማት ለማዋል እንጂ ማንንም ለመጉዳት አለመሆኑን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ሶሰቱም አገሮች አሸናፊ የሚሆኑበት መፍትሔ እንደምትሻ ገልጸዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብም በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ምንም አይነት ጉዳት እንደሌለው፤ ይልቁንም ጎርፍና ድርቅ የመከላከል ፋይዳ እንደሚኖረው አረጋግጠዋል።

'ለቴክኒካል ችግሮች ቴክኒካል መፍትሔ ያስፈልጋል' ያሉት ዶክተር ስለሺ፤ ኮሚቴው ከትክክለኛ ስምምነት ለመድረስ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መንጻት እንደሚገባውም ተናግረዋል።

የናይል ወንዝ ለሁሉም የሚበቃ ሰፊ ሀብት በመሆኑ ድርድሩ በአጠቃቀም እንጂ የውሃ ክፍፍል ዙሪያ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።

የግብጽ የውሃ ሚኒስትር መሃመድ አብደልአቲ ለኢትዮጵያዊያን መልካም የገና በዓል በበመኘት በጀመሩት ንግግራቸው፤ ከዚህ በፊት በተደረጉ የድርድር መድረኮች የተነሱ ልዩነቶችን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሚደረሰው ስምምነት ሶሰቱንም አገሮች ወደ ብልጽግና የሚወስድ መሆን እንደሚገባው ገልጸው፤አጠቃላይ የውሃ ሙሌትና አመራር ቴክኒካል ጉዳዮች በቅርብ ትብብርና ቅንጅት መምራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ግብጽ የውሃ እጥረት እንዳጋጠማት በመግለጽም፣ ግድቡ ግብጽን በማይጎዳ አኳሃን፣ በአስዋን ግድብ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ በማያስከትል መንገድ እንዲሆን እንደምትፈልግ አብራርተዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ውይይትም ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የሱዳን የውሃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ እስካሁን በርካታ ውይይቶችና ድርድሮች መካሄዳቸውንና በርካታ ጉዳዮች መነሳታቸውን አስታውሰዋል።

አሁን በውሃ አሞላልና አመራር ቴክኒካል ጉዳዮች የተጀመረው ድርድርም በትብብር መርህ ላይ የተመሰረተ የጋራ ስምምነት ላይ ሊያደርስ ይገባል ብለዋል።

ሱዳን የሶስቱንም አገሮች ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት እንደምትፈልግም አረጋግጠዋል።

ረጅም ጊዜ የወሰደው የሶስትዮሽ ድርድር፤ እንደ አዲስ ባሳለፍነው ህዳር ወር 2012 በአሜሪካ አደራዳሪነት በዋሽንግተን መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም