ቀጥታ፡

የኮሪያው የልማት ተራድኦ ለአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ትግበራ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው

ኢዜአ ታህስ 29/2012 የኮሪያው ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) የገቢዎች ሚኒስቴር ለሚተገብረው የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ። የገቢዎች ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክስ የአንድ መስኮት አገልግሎትን ታህሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በይፋ ማስጀመሩ ይታወሳል። የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት ስርዓት ለገቢ፣ ወጪና ተላላፊ እቃዎች የሚያስፈልጉ መረጃዎችና ሰነዶች በየሚመለከታቸው ተቋማት የሚደረግ የአካል ምልልስ ሳይኖር ባለበት ቦታ ሆነው አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ ስርዓት ነው። የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት የመጀመሪያ ምዕራፍ በገቢዎች ሚኒስቴር (በቀድሞው መጠሪያው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን) ከእ.አ.አ 2017 እስከ 2019 በሙከራ ደረጃ በ16 ተቋማት ሲተገበር ቆይቷል። ሚኒስቴሩ የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት የሙከራ ትግበራን ከሶስት ቀናት በፊት ወደ ሙሉ የተግባር ስራ ያስገባ ሲሆን እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። የኮይካ የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) የኢትዮጵያ ቢሮ ረዳት የፕሮግራም ሃላፊ አቶ ማቲዎስ ቡናሮ ለኢዜአ እንደገለጹት ኤጀንሲው ለአገልግሎቱ የሁለተኛ ምዕራፍ ትግበራ የ7 ነጥብ 49 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደርጋል። ከሚደረገው የፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪ ከደቡብ ኮሪያ በመጡ ባለሙያዎች የአገልግሎት ስርአቱን በየጊዜው የማሻሻልና ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል። የኮሪያ ዓለም አቀፍ የጉምሩክ ኤጀንሲ(ኩፒያ) በኤሌክትሮኒክስ የአንድ መስኮት አገልግሎት የመጀመሪያ ምዕራፍ ትግበራ ወቅት የአገልግሎት ስርአቱን የመዘርጋትና በየጊዜው እንዲሻሻል የቴክኒክ ድጋፎችን ማድረጉን ነው አቶ ማቲዎስ ያስታወሱት። ኮይካ አገልግሎቱ ውጤታማና የተቀላጠፈ እንዲሆንና የአገልግሎቱን አዋጭነት በመመልከት በሁለተኛው ምዕራፍ የአገልግሎት ትግበራ ላይ ድጋፍ ለማድረግ መግባቱንም ተናግረዋል። ለአገልግሎቱ የሶስተኛ ምዕራፍ ትግበራም ከወዲሁ የፕሮግራም ትግበራ ግምገማ በማድረግ ኤጀንሲው ፕሮጀክት እንደሚቀርጽም ጠቅሰዋል። ኮይካ በኢትዮጵያ የንግድ ስራ ምቹነት(ኢዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ) እንዲሻሻል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት የፋይናንስ ድጋፍም የዚሁ አካል እንደሆነ  ነው አቶ ማቲዎስ ያስረዱት። የደቡብ ኮሪያ መንግስት በቴክኖሎጂ ሽግግር ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ተስፋዬ በበኩላቸው መንግስት ለሁለተኛ ምዕራፍ የአገልግሎት ትግበራ 32 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው መግለጹን አስታውሰዋል። ከዚህም ውስጥ የኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ በመጠቆም። ድጋፉ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ የስጋት አመራር አስተዳደር፣ ለቅድመ መከላከልና ዝግጁነት እንዲሁም በዳታ ማዕከል ውስጥ የሚገኘውን መረጃ ለመተንተንና ለመጠቀም ለሚከናወኑ ስራዎች ይውላል ብለዋል። የሰርቨርና ለንግድ ስራዎች የሚውሉ ሶፍዌሮች ግዢና ጥገና ስራዎችም የድጋፉ አካል እንደሆነና የኢትዮጵያ ባለሙያዎችም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል። በፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምእራፍ ሙከራ ትግበራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ጨምሮ 16 ተቋማት መሳተፋቸውን ገልጸዋል። የኮሪያ ዓለም አቀፍ የጉምሩክ ኤጀንሲ (ኩፒያ) አገልግሎት ስርአቱን በማዘመን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የአገልግሎቱን ጥራት የማረጋገጥና የኔትወርክ መሰረተ ልማቱና የዳታ ማዕከሉ ደህንነትን የመጠበቅ ስራዎች በመጀመሪያው ምዕራፍ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አመልክተዋል። በሁለተኛው የአገልግሎት ምዕራፍ ትግበራ በመጀመሪያው ምዕራፍ ትግበራ ምዕራፍ ከነበሩት 16 ተቋማት በተጨማሪ ሌሎች 21 ተቋማት እንደሚካተቱም ጠቅሰዋል። በአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ሁለተኛ ምዕራፍ ትግበራ ከ150 እስከ 200 ሺህ ዜጎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አመልክተዋል። የመንግስትና ግል ባንኮች፣ የመንግስትና የግል የኢንሹራንስ ድርጅቶችና በሌሎች የንግድ ተቋማትም አገልግሎቱ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ለአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ሁለተኛ ምዕራፍ ትግበራ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙንና በወስጡም ስምንት ተቋማትን ያካተተ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ለአገልግሎት ትግበራው ለሚያስፈልገው በጀት ከኮይካ በተጨማሪ የልማት አጋሮች ድጋፍንም እንደሚያካትት አመልክተዋል። የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት በመንግስት በኩል በሶስት ምዕራፍ ለመተግበር መታሰቡንና አገልግሎቱን በዘላቂነት የማስፋት እቅድ እንዳለም አክለዋል። የኤሌትሮኒክስ አገልግሎቱ የንግድ ስራ ምቹነትን(ኢዝ ዱዊንግ ቢዝነስ) ለማሻሻል መንግስት እየሰራ ያለው ስራ አካል ነው። የዓለም ባንክ ግሩፕ በህዳር ወር 2012 ዓ.ም የንግድ ስራ ምቹነት ከባባቢያዊ ሁኔታን በሚመለከት ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ከ190ኛ አገራት 159ኛ ላይ አስቀምጧታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም