ቀጥታ፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ጉዳይ የሶስትዮሽ ውይይት ዛሬና ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ኢዜአ፤ ታህሳስ 29/2012 የኢትዮጵያ ፣ግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ጉዳይ ላይ የሚያተኩረውን ስብሰባቸውን ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ያካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአሜሪካ ጋባዥነት ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን ባደረጉት ስብሰባ አገራቱ በግድቡ ዙሪያ አራት የቴክኒክ ስብሰባዎችን በማድረግ እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ከስምምነት ላይ ለመድረስ ቀነ ገደብ አስቀምጠው ነበር።

በዚሁ መሰረት ሶስት የቴክኒክ ስብሰባዎች በአዲስ አበባ፣ ካይሮና ካርቱም ተካሂደዋል።

የመጨረሻው ስብሰባም ዛሬ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሶስቱ አገራት በዋሽንግተን ዲሲ በደረሱት ስምምነት በእስካሁኖቹ የቴክኒክ ስብስባዎች ላይ አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም እና ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን ለመሰብሰብ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ የዛሬ ወር ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም ተካሂዷል።

ተከታዩን ስብሰባቸውን ደግሞ በመጪው ሳምንት ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሶስቱ አገራት በዋሺንግተን ዲሲ በደረሱት ስምምነት አማካኝነት እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ስምምነት ላይ ካልደረሱ እ.አ.አ ካርቱም ላይ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ የተፈረመው ስምምነት አንቀጽ 10 ተግባራዊ እንዲሆን ይደረጋል።

የካርቱም የመርሆዎች ስምምነት 10 አንቀጾች የያዘ ሲሆን የመጨረሻው አንቀጽ 10፤ "ሶስቱ አገራት በመርሆዎች ስምምነቱ አተረጓጎምና ተግባራዊነት የተነሱ አለመግባባቶችን በውይይት ወይም በድርድር ይፈታሉ፤ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን አደራዳሪ ሊጠይቁ ወይም ለአገራቸው ርዕሳነ ብሔሮችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሊያሳውቁ ይችላሉ" ይላል።

ሶስተኛው የሶስቱ አገራት የቴክኒክ ስብሰባ ታህሳስ 11 እና 12 ቀን 2012 ዓ.ም በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም መካሄዱ የሚታወስ ነው።

በካርቱም የተካሄደው ውይይት የግድቡ የውሃ አሞላል ሂደት፣ የውኃ አለቃቀቅ፣ ከሙሌት በኋላ ያለው የግድቡ ኃይል የማምረት ተግባርና ድርቅ ቢከሰት የወንዙን ውሃ እንዴት ማስተዳደር ይቻላል የሚሉት ርእሰ ጉዳዮች ይገኙበታል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የካርቱሙ ውይይት ተከትሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከዚህ በፊት የግድቡ ውሃ አሞላልንና ዓመታዊ ፍሰትን ጨምሮ በግብጽ በኩል የቀረቡት የመደራደሪያ ሀሳቦች እንዲነሱ መደረጉን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ግብጽ አቅርባው በነበረው ሀሳብ አማካይ ዓመታዊ የውሃ ፍሰት 49 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር እንዲሆን፤ እንዲሁም የአስዋን ግድብ ከፍታ 165 ሜትር እንዲጠበቅ የሚሉት ይገኙበታል።

ግብጽ ተፈጥሯዊ ፍሰት የሚል አዲስ መደራደሪያ ሀሳብም አቅርባ እንደነበር ሚኒስትሩ አስታውሰው ይህም በኢትዮጵያ በኩል ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ እንዲቀር መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም