ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ጊኒ አቀኑ

ኢዜአ ታህሳስ 28/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ወደ ጊኒ ኮናክሬ አምርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጊኒ በተጨማሪ በኢኳቶሪያል ጊኒና ደቡብ አፍሪካ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊኒ ኮናክሬ በሚኖራቸው ቆይታ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አልፋ ኮንዴ ጋር አገራቱ ባላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ እንደሚወያዩ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢዜአ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አልፋ ኮንዴ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት እና በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። የመጀመሪያው የኢትዮ-ጊኒ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ምስረታ ስብሰባ ላይም ፕሬዚዳንቱ የተሳተፉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ስትራቴጂያዊ አጋርነት የሚመሰርት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ተቋቁሟል። የሁለቱ አገራት መሪዎች በተገኙበት ስትራቴጂክ አጋርነትን የሚያጠናክሩ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን መመስረቻ ስምምነት በተጨማሪም በትምህርት፣ ጤና፣ በገንዘብና ማኔጅመንት፣ በግብርና እንዲሁም በባህልና ቱሪዝም መስኮች ለመተባበር የሚያስችል ስምምነቶች መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የጊኒ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለተመሳሳይ ዓላማ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ እንደሚያቀኑና ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቲኦዶሮ ኦቢያንግ ጋርም በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ነው አቶ ንጉሱ የገለጹት። የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ቲኦዶር ኦቢያንግ በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገው ነበር። በዚህ ወቅትም አገራቱ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በመከላከያ ትብብርና ሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጉብኝታቸው በኋላ ጥር 3 እና 4 ቀን 2012 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፖሳ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) 108ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ እንደሚታደሙም አቶ ንጉሱ አመልክተዋል። ደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋርም በጁሃንስበርገ 34 ሺህ ህዝብ በሚያስተናግደው ኢምፔሪያል ዋንድረርስ የክሪኬት ስታዲየም ውይይት እንደሚያደርጉም ነው አቶ ንጉሱ ያብራሩት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጆሃንስበርግ ለሚያደርጉት ጉብኝት አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የከተማዋ  ከንቲባ ጂኦፍ ማክሁቦ መግለፃቸውን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ አመልክቷል። የከተማው ከንቲባም ጂኦፍ ማክሁቦ በኢትዮጵያዊያኑ የውይይት መድረክ ላይ በመገኘት ለኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም