ቀጥታ፡

የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በመጪው ቅዳሜ ይጀመራል

ኢዜአ ታህሳስ 28/2012 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በመጪው ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም ይጀመራል። በሁለቱም ጾታዎች በሚካሄደው የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር በሴት ስድስት በወንድ አምስት ክለቦች ይሳተፋሉ።

ጎንደር ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን፣ ሀዋሳ ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማ እና አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ጅማ ከተማ በሴቶቹ የሚሳተፉ ክለቦች ሲሆኑ፣

ሀዋሳ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ጎንደር ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማና አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ አጋዚ ውቅሮ በወንዶች ተሳታፊ ክለቦች ናቸው።

የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ጥር 2 እና 3 ቀን 2012 ዓ.ም በክልል ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል።

በዚሁ መሰረት በሴቶች ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከየካ ክፍለ ከተማ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

እሁድ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ከጠዋቱ 3 ሰአት፤ ጅማ ላይ ጅማ ከተማ ከአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከረፋዱ 4 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በወንዶች ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከየካ ክፍለ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰአት፤ እሁድ ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰዓት የሚጫወቱ ይሆናል።

በባለፈው ዓመት በሊጉ በወንዶች ተሳታፊ የነበሩት አዳማ ከተማና ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት በበጀት ችግር ምክንያት በዘንድሮው የውድድር ዓመት አይሳተፉም።

በሴቶች አምና ተሳታፊ የነበረው ፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተጫዋቾች ለውድድሩ ባለማዘጋጀቱ ምክንያት በዘንድሮው የውድድር ዓመት እንደማይሳተፍ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ የውድድር ዓመት ነው።

ሀዋሳ ከተማ በወንዶች ጎንደር ከተማ በሴቶች የባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም