ይርጋጨፌ ወረዳ የጌዴኦ ዞን የባህል ስፖርት አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ይርጋጨፌ ወረዳ የጌዴኦ ዞን የባህል ስፖርት አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ
ኢዜአ ታህሳስ 28/2012፡ - በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የሰነበተው የባህል ስፖርት ውድድር ተጠናቀቀ፡፡ ውድድሩ ትላንት ሲጠናቀቅ እንደተገለጸው የባህል ስፖርት ውድድር የአሁኑን ጨምሮ በዞን ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ ተካሄዷል። በዚህኛው ውድድር ከሶስት የከተማ አስተዳደሮች እና ከስምንት ወረዳዎች የተወጣጡ 300 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። የገና ጨዋታ፣ ገበጣ ፣በሻህ ፣በቡብ ፣ትግልን ጨምሮ አስር የስፖርት ዓይነቶች በውድድሩ የተካሄዱ ናቸው። ይርጋጨፌ ወረዳ አጠቃላይ አሸናፊ የሆነው በእነዚህ ውድድሮች አብዛኛውንን በማሸነፉ ባስመዘገበው ውጤት ነው። የዞኑ ባህል ፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ የምስራች ዳካ እንዳሉት ውድድሩ በባህል ስፖርቶች ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣቶች ማየት ተችሏል። ከዚህ ባለፈም የውድድሩን ህግ በመጠበቅና ስፖርታዊ ጨዋነትን በማክበሩ ረገድ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ እንቅስቃሴ እንደነበር አመልክተዋል። በቀጣይ በክልል ደረጃ ዞኑን የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞችን መመረጣቸውንም አስታውቀዋል። የገደብ ወረዳ የገና ጨዋታ ስፖርተኛ ወጣት እርቅሁን በቀለ በሰጠው አስተያየት "የባህል ስፖርት ከውድድር ባለፈ የራሳችንን ባህል ጠንቅቀን እንዲናውቅ እድል የፈጠረ ነው "ብሏል። ለባህል ስፖርት የሚሰጠው ዝቅተኛ ትኩረት በዘርፉ የሚሳተፉ ታዳጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንዲመጣ አመልክቷል። "ለስፖርቱም ትኩረት በመስጠት ከትውልድ ወደ ትውልድ ከማሸጋገር ባለፈ ለተቀረው አለም ለማስተዋወቅ ሊሰራ ይገባል " ብሏል። ከይርጋጨፌ ወረዳ የመጠው ወጣት ብርሃኑ ሆርዶፎ በበኩሉ የባህል ስፖርት በአንድ ወቅት ውድድር ብቻ ተገድቦ መቅረቱ እድገት ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳደር ተከታታይነት እንዲኖረው ታዳጊዎችን ማፍራትና የማዝውተሪያ ስፍራዎችን መስፋፋት እንደሚገባ ጠቁሟል። በመዝጊያው "ለት በገና ጨዋታ ወንዶች ገደብ ወረዳ የኮቾሬ አቻውን አሸንፏል። ለአሸናፊ ስፖርተኞችና ወረዳዎች የዋጫና የሜዳልያ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን በአጠቃላይ ይርጋጨፌ እና በስፖርታዊ ጨዋነት ደግሞ ኮቾሬ ወረዳ አሸናፊ ሆነዋል።