የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ
ኢዜአ ታህሳስ 27 /2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታዎች ነገ ታህሳስ 28 እና ታህሳስ 29 ቀን 2012 ዓም ይካሄዳሉ። የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ከተጀመረ 7ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ታህሳስ 28 እና ታህሳስ 29 ቀን 2012 ዓም የሚቀጥሉ ሲሆኑ ሁሉም በክልል ስታዲየም የሚካሄዱ ይሆናሉ። በዚህም መሰረት ነገ ታህሳስ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ስሁል ሽረ ከሰበታ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር ከወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና ከሲዳማ ቡና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በተከታዩ ቀን ረቡዕ በሚደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ወላይታ ድቻ ከፋሲል ከነማ፣ መቀለ 70 እንደርታ ከአዳማ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ጋር ይጋጠማሉ። ፕሪሚየር ሊጉን ፋሲል ከነማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በእኩል 11 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን መቀለ ሰብአ እንደርታ በ10 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ቡና፣ ሲዳማ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በተመሳሳይ 9 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበላልጠው ከአራት እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዘው ይከተላሉ። ስሁል ሽረ፣ ወላይታ ድቻ እና ሃድያ ሆሳእና ደግሞ በሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል። የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ6 ጎል እየመራ ሲሆን ማማዱ ሲዲቤ እና ፍጹም አለሙ ከባህርዳር ከተማ፣ እንዳለ ከበረ ከኢትዮጵያ ቡና፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመቀለ ሰብአ እንደርታ፣ ብሩክ በየነ ከሃዋሳ ከተማ እንዲሁም አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና በ4 ጎሎች ይከተላሉ።