ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ በበዓል ሰሞን ሐሰተኛ የገንዘብ ዝውውር ሊኖር ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት - አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

አዲስ  አበባ ታህሳስ 27/2012 ህብረተሰቡ በበዓል ሰሞን ሐሰተኛ የገንዘብ ዝውውር ሊኖር ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ የገና በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም ገልጿል። አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ በበዓል ሰሞን የሀሰተኛ ገንዘብ ዝውውር ሊኖር እንደሚችል ህብረተሰቡ ሆነ የፋይናንስ ተቋማት ተገንዝበው ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገ አስታውቋል። በቅርቡ አንድ ግለሰብ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገርጂ ቅርንጫፍ 7 ሀሰተኛ ባለ መቶ ብር ኖቶችን ከ26 ሺህ ብር ጋር በመቀላቀል ገቢ ለማድረግ ሲሞክር ባንኩ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ መያዙን አውስቷል። ሁልጊዜም ቢሆን ህብረተሰቡ በበዓል ጊዜ የሐሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውር እንደሚኖር ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ተመልክቷል። ኮሚሽኑ የገና በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱንም ገልጿል። የገና በዓል ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ኮሚሽኑ ለወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ልዩ ትኩረት በመስጠትና እቅድ በማውጣት ሙሉ የሰው ሃይሉን በማሰማራት ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ነው በመግለጫው የተጠቆመው። ከወትሮ በተለየ መልኩ በበዓል ዋዜማና በበዓል ዕለት ግብይት እና መዝናናት እንደሚጨምር ታሳቢ በማድረግ በገበያና በመዝናኛ ስፍራዎች እንዲሁም በከተማችን በተለያዩ አካባቢዎች የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰትና ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቼ እየሰራሁ ነው ብሏል። ህብረተሰቡ የፀጥታ ጉዳይ የጋራ መሆኑን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ እንደሚገኝና ከዚህ ቀደም የተከበሩ ሃይማኖታዊም ሆኑ ብሄራዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ነዋሪው ከፍተኛ ድርሻ ማበረከቱ የሚታወቅ ሲሆን ህዝቡ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል። ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ መረጃ ለመስጠት በነፃ የስልክ መስመር 991 እና 816 ወይም በ011- 1 -11- 01 -11 መጠቀም እንደሚችል ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለሚያከናውናቸው ተግባራት ስኬታማነት ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ቀና ትብብር ምስጋናውን አቅርቦ በዓሉ የሰላም፣የደስታና የስኬት እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም