ቀጥታ፡

ሃይማኖታዊ የአደባባይ ክብረ በዓላት የህዝብን አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ በመሆናቸው ሊጠበቁ ይገባል ተባለ

ታህሳስ  27/2012 ጥምቀትንና ኢድ -አልፈጥርን ጨምሮ ህዝብ በጋራ የሚታደምባቸው ሃይማኖታዊ የአደባባይ ክብረ በዓላት የተለያዩ ማህበረሰቦችን አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ በመሆናቸው ሁሉም ሊጠብቃቸው ይገባል ተባለ። ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች፣ የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ሌሎችም ልዩነቶችን አቻችለው በመከባበርና በመተሳሰብ በአንድነት የሚኖር ህዝብን የያዘች አገር ናት።

የአገሪቱ ዜጎች በተለይ ሃይማኖታዊ በዓላት ሲመጡ ሃይማኖትንና ቋንቋን የመሳሰለው የልዩነት መስመር ሳይገድባቸው በጋራ የማክበር ልዩ ባህልን የተጎናፀፉ መሆናቸውም የተለየ ያደርጋቸዋል።

የማህበረሰብ ጉዳይ ጥናቶች እንደሚሉት በኢትዮጵያ የቆየው አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ እሴት አገሪቱ አንድ ሆና እንድትቆይ ያደረገ በመሆኑ አገራዊና ማህበረሰባዊ ፋይዳው የጎላ ነው።

በመሆኑም በኢትዮጵያዊያን ዘንድ በስፋት የሚታወቀው አብሮነትና አንድነት በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ሳቢያ እንዳይሸረሸር መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን የአገራቸው ጉዳይ የሚቆረቁራቸው አንዳንድ ወጣቶች ይናገራሉ።

ከወጣቶች መካከል አወቀ ምትኩ ናወጣት ረቢፈል አሰፋ  እንዳሉት በተለይም በአደባባይ የሚከወኑ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት የሙስሊም ክርስቲያኑን ህዝብ የአንድነት፣ የመተባበርና የመተጋገዝ ባህን ይበልጥ የሚያሳድግ ነውም ይላሉ። በመሆኑም ሁሉም ሊጠብቀው ይገባል የሚል ማሳሰቢያ በማከል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እንደገና ደሳለኝ በበኩላቸው በአደባባይ የሚከወኑ ክብረ በዓላት ለቱሪዝም የሚያስገኙት ገቢ፣ የሚፈጥሩት የስራ እድል እንዲሁም በአገር ገጽታ ላይ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባሻገር የጋራ አንድነት መገለጫም ጭምር ናቸው ይላሉ።

የአገሪቱን አንድነት በማጠናከር የሰላም ፀር የሆኑ ተግባራትን ለመከላከል የሚያግዙትን ክብረ በዓላት መጠበቅ ግድ ነው ባይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ብጹእ አቡነ አረጋዊ (ዶክተር) ጥምቀትን የመሳሰሉ የአደባባይ ክብረ በዓላት የሚያንፀባርቁት መልዕክት ፋይዳው ከአገር አልፎ የሚዘልቅ መሆኑን ይገልፃሉ።

ይህም ሃብትነቱ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንና የአለምም ህዝብ ጭምር መሆኑን በማከል።

በመሆኑም ህዝቡ እንደነዚህ ዓይነት በዓላትን በአንድነት፣ በመከባበርና በመፈቃቀር ሊጠብቃቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም