በሰሜን ሸዋ ዞን የሚከወኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የአደባባይ ከብረ በዓላትን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን የሚከወኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የአደባባይ ከብረ በዓላትን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2012 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚከወኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የአደባባይ ክብረ በዓላት ለጎብኝዎች መዳረሻ ይሆኑ ዘንድ በስፋት የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ዞኑ አስታወቀ። የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት መኳንቴ በተለይም ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት በስፋት ይከናወናሉ። በተያዘው ዓመት የሸዋን ታሪክና እሴቶች ለማስተዋወቅ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ትልቅ ፕሮጀክት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል። የገና ጨዋታና የጥምቀት ክብረ በዓላት በዞኑ ከሚከወኑ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ እሴቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ጎብኝዎች መዳረሻ እንዲሆኑ የማስተዋወቅ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አክለዋል። በዚህ ዓመትም የክብረ በዓላቱ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ስርዓቱን በርካታ መገናኛ ብዙሃን የፕሮግራም ቀረጻዎች ማድረጋቸውን ለአብነት አንስተዋል። በዞኑ ከሚገኙ የጥምቀት አከባበር ስርዓቶች መካከል በኢትዮጵያ ብቸኛው ከ50 በላይ ታቦታት በአንድ ባህረ ጥምቀት ስርዓተ ጥምቀት የሚከወንበት ስርዓት በምንጃር ሸንኮራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ በሰሜን ሸዋ በአንድነት፣ በመቻቻልና በፍቅር በልዩ ሁኔታ ከ400 ዓመታት በፊት ጀምሮ የሚከናወነውን የምንጃር ሸንኮራ የጥምቀት በዓል አከባበርን ለጎብኝዎች ተደራሽ እንዲሆን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጠር አብራርተዋል። በሌላ በኩል ከገና በዓል ጋር ተያይዞ የሚከወኑ ባህላዊ ጨዋታዎች በዞኑ በርካታ ስፍራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመትም በርካታ ሚዲያዎች ባህላዊ ስርዓቶች በስፋት ለማስተዋወቅ በተለያዩ ስፍራዎች ተገኝተው ቀረጻ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል። ከሁሉም ክብረ በዓላት በተጨማሪ በሰሜን ሸዋ በርካታ ህዝብ የሚታደምባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታዊ የንግስ በዓላት እንደሚደረጉ አንስተዋል። ለአብነትም በየዓመቱ ጥር ሰባት በጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን የደብረ ብርሃን ስላሴ የሚደረገው ሃይማኖታዊ በዓል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከብረ በዓሉና ቤተ ክርስቲያኑ ያቀፏቸውን ጥንታዊ ቅርሶች ጎን ለጎን የማስተዋወቅ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።