በዲላና ይርጋጨፌ የበዓል ገበያው የተረጋጋ መሆኑን ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በዲላና ይርጋጨፌ የበዓል ገበያው የተረጋጋ መሆኑን ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናገሩ
ኢዜአ፤ ታህሳስ 27/2012 የበዓል ገበያው የተረጋጋና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ የሌለበት መሆኑን በጌዴኦ ዞን ዲላና ይርጋጨፌ ከተሞች አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።
በጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ ደግሞ በአንዳንድ የግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደለ ተመልክቷል።
የዲላ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ኤደን አሸናፊ እንዳሉት ለበዓል የሚሆን ፍጆታ ለመሸመት ገበያ ወጥተው ቀይ ሽንኩርት 15 ብር ፣ቲማቲም 18 ብር እና ቅቤ ደግሞ 230 ብር በኪሎ ገዝተዋል።
ካለፉት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የበዓል ገበያ አንጻር ሲታይ የዋጋ ጭማሪ ቢኖረውም የተጋነነ አለመሆኑን ተናግረዋል።
የቁም እንስሳት ገበያ ማዕከል መካከለኛ በሬ ከ20 እስከ 25 ሺህ እንዲሁም ከፍተኛው ደግሞ እስከ 30 ሺህ ብር ሲሸጥ መመልከታቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ አስቻለው ዋርካ ናቸው።
እንደ አቶ አስቻለው ገለጻ ዋጋው በዳልጋ ከብት ገበያ ላይ ጭማሪ አሳይቷል።
የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት ቀነኒ ገመዳ በበኩላቸው የበዓል ገበያው የተረጋጋ መሆኑን ገልጸው "እንቁላል አንዱ አራት ብር ፣ ዶሮ ደግሞ ከ200 እሰከ 350 ብር እየተሸጠ ነው "ብለዋል።
በዲላ ከተማ በንግድ ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ ፋጡማ ማሀመድ ሽንኩርትን ጨምሮ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ እንደሚገኙና የተጋነነ ጭማሪ እንደሌለ ተናግረዋል።
የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሰላም አየለ እንዳሉት የገና በዓልን ተከትሎ ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ቁጥጥር እየተደረገ ነው።
እስካሁን ባለው የግብይት ሂደት ችግር እንዳላጋጠመ ጠቁመው ከልኬት ጋር ተያይዞ ፍተሻ በማድረግ ችግር ያለባቸውን ሚዛኖች እንዲሰበሰቡ መደረጉን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል በነገሌ ከተማ በበዓሉ ገበያ በቂ አቅርቦት ቢኖርም በአንዳንድ ግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ሸማቾች አመልክተዋል፡፡
ከሸማቹች መካከል ወይዘሮ አለሚቱ ሸጋው በሰጡት አስተያየት በቀዳሚው ሳምንት በኪሎ 18 ብር የነበረውን ቀይ ሽንኩርት በ20 ብር፤ 15 ብር የነበረውን ቲማቲም 18 ብር መሸመታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌሎችም የግብርና ምርቶች ላይም ጭማሪ መታየቱን አመልክተዋል፡፡
ሌላዋ ሸማች ወይዘሮ አለምጸሀይ ተሾመ በበኩላቸው የተጋነነ ባይሆንም በሸቀጣ ሸቀጦችና አንዳንድ የግብርና ምርቶች ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ እንዳለ መታዘባቸውን ገልጸዋል።
የጉጂ ዞን ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ ኡዶ ፍትሀዊ የንግድ ውድድርን ለማስፈንና ገበያን ለማረጋጋት በየወረዳው የክትትልና ቁጥጥር ግብረኃይል መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
ተጠቃሚውን የሚጎዳ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴች ከገንዘብ እስከ ፈቃድ መሰረዝ የሚያደርስ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስረድተዋል፡፡
"ግብረሀይሉ ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ በሚካሄድባቸው ነገሌ አዶላና ሻኪሶን ጨምሮ በዞኑ 14 ዋና ዋና ከተሞች የክትትልና ቁጥጥር ስራውን አጠናከሮ ቀጥሏል "ብለዋል፡፡