ቀጥታ፡

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር አሸናፊ ሆነ

ኢዜአ ፤ ታህሳስ 27/2012 ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር አሸናፊ ሆነ።

ከታህሳስ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው የአቋም መለኪያ ውድድር ትናንት ፍጻሜውን አግኝቷል።

በውድድሩ ላይ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብና ወላይታ ሶዶ ዩንቨርሲቲ ተሳትፈዋል።

ትናንት በውድድሩ መዝጊያ ቀን በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ጨዋታዎችን ያሸነፉት ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካና ፌደራል ማረሚያ  ቤቶች ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በጨዋታው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጋጣሚውን 3 ለ 2 በማሸነፍ የአቋም መለኪያ ውድድሩ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጨዋታውን ያሸነፈው ከ2 ለ 0 ከመመራት ተነስቶ ነው።

ከትናንት በስቲያ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብና ወላይታ ሶዶ ዩንቨርሲቲ ባደረጉት ጨዋታ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 ተጋጣሚውን በማሸነፍ ሶስተኛ ወጥቷል።

የሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር የተዘጋጀው ለሴት የቮሊቦል ክለቦች የውድድር አማራጭ መፍጠርና ፕሪሚየር ሊጉ ከመጀመሩ በፊት አቋማቸውን እንዲፈትሹ ነው።

የሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት ተካሄደዋል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል።

መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 በተመሳሳይ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣና ባህርዳርን በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 አሸንፈዋል።

በክልል ከተማ ሙገር ላይ ሙገር ሲሚንቶ ፌደራል ማረሚያ ቤቶችን በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 0 አሸንፏል።

ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ከመከላከያ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም የሶዶ ሜዳ ለሌላ አገልግሎት በመያዙ ጨዋታው ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ሙገር ሲሚንቶ በ10 ነጥብ ሲመራ፣አዲስ አበባ ፖሊስ በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛ መዳወላቡ ዩንቨርስቲና ወላይታ ድቻ በተመሳሳይ ስምንት ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በተጨማሪም ትናንት እና ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

ትናንት ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማና ጎንደር ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 25 ለ 25 በሆነ የአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ፌደራል ማረሚያ ቤቶችን 22 ለ 18 አሸንፏል።

በፕሪሚየር ሊጉ ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሶስት ጨዋታዎች ተደርገዋል።

የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አዲስ ተሳታፊውን ሚዛን አማንን 48 ለ 22፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መከላከያን 24 ለ 23 እና መቐለ ሰብዓ እንደርታ ፌደራል ፖሊስን 29 ለ 23 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም