ቀጥታ፡

በምርምር የተገኙ የስንዴ ዝርያዎች በግል ተቋማት እንዲባዙ ድጋፍ አደረጋለሁ፡-የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት

ኢዜአ  ታህሳስ 25/2012  የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት  የምርምር ውጤቶችን ከማፍለቅ ባለፈ በምርምር የተገኙ ዝርያዎች በግል ተቋማት እንዲባዙ ድጋፍ  እንደሚያደረግ  ገለጸ፡፡ የደጋማ እና ወይናደጋማ አየር ንብረት ምርት ተብሎ የሚታወቀው ስንዴ በቆላማ የአገሪቷ ክፍልም በመስኖ መልማት መቻሉን መሬታቸውን በዓመት ሁሉት ጊዜ በዘር በመሸፈን ያረጋገጡ የአካባቢው አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ረጅም እቅድ ሰንቀዋል። ኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ፍጆታዋ ከ67 ሚሊየን ኩንታል በላይ ሲሆን በሀገር ውስጥ ምርት የሚሸፈነው 75 በመቶው ብቻ ነው። ቀሪውን ከውጭ በማስገባት ለመሸፈንም አገሪቷ በየዓመቱ  ከ600 እስከ 700 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማውጣት እንደምትገደድ መረጃዎች ያመለከታሉ። ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ለመተካት ከከፍተኛ ቦታዎች በተጨማሪ እንደ አዋሽ፣ ኦሞና ዋቢ ሸበሌ ባሉ የተፋሰሱ ቆላማ አካባቢዎች የቆላ ስንዴ በመስኖ ለማመረት እንቅስቃሴ ጀምራለች። ከኦሮሚያ ክልል ጊንጪ ተነስቶ መዳረሻው አፋር ክልል አፋምቦ በረሃ ባደረገው አዋሽ ተፋሰስ አካባቢ ያሉ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ደግሞ የቆላ ስንዴ ማምረት ጀምረዋል። በአፋር ክልል አፋምቦ፣ አሚባራ፣ አሳይታ፣ ዱብቲ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ጀጁ፣ መርቲ፣ ፈንታሌ ወረዳዎች ያሉ ነዋሪዎች የቆላ ስንዴ በመስኖ የሚያመርቱባቸው ቦታዎች ናቸው። አምራቾቹ ለኢዜአ እንገለጹት "ስንዴ በመኪና ተጭኖ ሲመጣ እንጂ ሲመረት አይተው አያውቁም"፤ አሁን ግን ራሳቸው በማምረት ከራሳቸው አልፈው ለአገሪቷም ሊበቁ ነው። መንግስት መሬቱን በትራክተር እያሳረሰላቸው መሆኑን የገለፁት አምራቾቹ የማዳበሪያ፣ የጸረ አረም መድሃኒት የመሳሰሉትን ግብዓቶች እንደሚያቀርብላቸውም ገልጸዋል። በቀጣይም መንግስት "ከእኛ አቅም በላይ" ያሉትን ግብዓት የሚያቀርብላቸው ከሆነ በስፋት በማምረት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ በልበ ሙሉነት ይገልጻሉ። ስንዴ ማምረት እንደምንችል አሳይተውናል የሚሉት አርሶ አደሮቹ፤ ስራችን ቀጣይነት አንዲኖረው የመንግስትን ድጋፍና ክትትል እንሻለን ብለዋል። የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ መገርሳ በበኩላቸው በአዋሽ ተፋሰስ ብቻ መልማት የሚችል ከ 206 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ማልማት ይቻላል ብለዋል። በተፋሰሱ ብቻ ማልማት ቢቻል ሃገሪቷ ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት በግማሽ መቀነስ እንደሚቻልም ገልጸዋል። በመሆኑም ተፋሱስ በሚያልፍባቸው የኦሮሚያና አፋር ክልሎች ለዘርና ለምግብነት የሚያገለግል የቆላ ስንዴ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል። የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል በሁለት ሺህ 500 ሄክታር፤ በማህበራት ደግሞ አንድ ሺህ 700 ሄክታር ለዘር የሚሆን ስንዴ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል። በተፋሰሱ መልማት ከሚችለው መሬት እየለማ ያለውም ከሁለት በመቶ እንደማይበልጥ የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ በቅንጅት መስራት የቀጣይ ስራ መሆን አለበት ብለዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችን በምርምር ከማፍለቅ ባለፈ ዝርያዎችን የሚያባዙ አካላት እንዲደራጁ እናደርጋለን ብለዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ከደጋማ አካባቢዎች ባለፈ ለቆላ ስንዴ ምረት የሚያገለግሉ ፈንታሌ 1፣ ፈንታሌ 2፣ ቀቀባ፣ ደንደአ፣ ጋምቦ፣ አሚባራና ሌሎችም የስንዴ ዝርያዎችን አውጥቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም