ቀጥታ፡

የኦሮሚያ ክልል የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ

ኢዜአ ታህሳስ 25/2012 የኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። ከታህሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮናው ዛሬ ተጠናቋል። በሻምፒዮናው በሁለቱም ጾታዎች ከአማራ ክልል ውጪ ስምንቱ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተሳትፈዋል። በተጨማሪም ከአማራ ክልል የደብረ ብርሃንና የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላትም የተሳተፉ ሲሆን፤ ወንድ 176 ፣ ሴት148 በድምሩ 324 አትሌቶች በሻምፒዮናው ላይ ተሳትፈዋል። ሻምፒዮናው ከ18 ዓመት እና ከ16 ዓመት በታች በሚል በሁለት የእድሜ ዘርፎች የተካሄደ ነው። ከ18 ዓመት በታች ላይ እድሜያቸው 16 እና 17 የሆኑ አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከ16 ዓመት በታች ላይ እድሜያቸው 15 የሆኑ አትሌቶች ተሳትፈዋል። የሻምፒዮናው ዓላማ ለፕሮጀክት አትሌቶች የውድድር እድል መፍጠር እንደሆነም ተገልጿል። የኢትዮጵያ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ሲጠናቀቅ ሰባት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሂደዋል። በሻምፒዮናው በተመዘገቡ ውጤቶች የሁለቱ ጾታዎች አሸናፊና አጠቃላይ የሻምፒዮናው አሸናፊ ተለይተዋል። በዚሁ መሰረት በወንዶችና በሴቶች የኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ሲሆን፤ በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ ደብረብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሁለተኛ የትግራይ ክልል ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በአጠቃላይ ድምር ውጤትም የኦሮሚያ ክልል የሻምፒዮናው አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ባለቤት ሲሆን፤ ደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከልና የትግራይ ክልል ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል። ለተወዳዳሪዎች የተዘጋጀውን የዋንጫ ሽልማት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ የአሰላ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ከድርና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አበርክተዋል። በሻምፒዮናው ላይ የአማራ ክልል ያልተሳተፈ ሲሆን፤ ክልሉ በሻምፒዮናው ላይ ያልተሳተፈበትን ምክንያት አለማሳወቁን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መግለጹ የሚታወስ ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም