ቀጥታ፡

የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል

የአምናው የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የውድድር ዓመቱን በድል ጀምሯል። የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎች ተጀመረ። ፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ ሲጀመር በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሶስት ጨዋታዎች ተደርገዋል። የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከአዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ኮልፌ ተጋጣሚውን 48 ለ 22 በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፏል። ፍጹም የአንድ ቡድን የበላይነት በታየበት በዚህ ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጨዋታውን በጣም በቀላል ሁኔታ ያሸነፈ ሲሆን በጨዋታው ከዚህ በላይ ግቦችን አስቆጥሮ ማሸነፍ ይችልም ነበር። የሚዛን አማን የእጅ ኳስ ክለብ በኳስ አወራወር፣ በመከላከል፣ በቦታ አያያዝና ያገኙትን የግብ አጋጣሚ ከመጠቀም አኳያ ሰፊ የቴክኒክ ችግር ታይቶባቸዋል። ጨዋታው ሚዛን አማን በፕሪሚየር ሊጉም ተፎካካሪ ለመሆን ጊዜ እንደሚፈልግና ልምድ ማካበት እንዳለበት ያመላከተ ነው። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ የውድድር ጨዋታ ነው ለማለት የሚያስችል አልነበረም። በመሆኑም የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የውድድር ዓመቱን በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ጀምሯል። ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከመከላከያ ጋር ያደረጉት ጨዋታ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 24 ለ 23 አሸናፊነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በከፍተኛ ሁኔታ ሃይል የተቀላቀበለት ሲሆን ዳኞች በተደጋጋሚ ጊዜ የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ሲሰጡም ታይቷል። በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተወሰነ ብልጫ በመውሰድ ጨዋታውን በአምስት የነጥብ ልዩነት መምራት የቻለ ቢሆንም መከላከያ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግቦችን በማስቆጠር ልዩነቱን በአንድ አጥብቧል። የጨዋታው ኮከብ የሚያስብለውን ብቃት ያሳየው የቂርቆስ ክፍለ ከተማው ተጫዋች መሐመድ ከድር 13 ግቦችን ማለትም ቡድኑ ካገባቸው ግቦች ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። በመከላከያ በኩል ጥሩ ብቃት ያሳየው ወንደሰን አለማየሁ ሰባት ግቦችን አስቆጥሯል። ፌዴራል ፖሊስ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ያደረጉት ጨዋታ በመቐለ ሰብዓ እንደርታ 29 ለ 23 አሸናፊነት ተጠናቋል። በሁለቱ ክለቦች መካከል በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየ ሲሆን ጨዋታው 13 ለ 13 በሆነ የአቻ ውጤት ነበር የተጠናቀቀው። በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ መቐለ ሰብዓ እንደርታ የጨዋታ ብልጫ የወሰደ ሲሆን በአንጻሩ ፌደራል ፖሊስ ተዳክሞ ታይቷል፤ ያገኛቸውን የግብ እድሎችንም በአግባቡ መጠቀም አልቻለም። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት  ሃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ባለፈው ዓመት የታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች እንዳይደገሙ ሁሉም ሃላፊነት ወስዶ ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል። ፌደሬሽኑ ስፖርታዊ ጨዋነትን የሚጥሱ ተግባራትን የሚያከናውኑ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድም አመልክተዋል። ጨዋታዎችን በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት ለማካሄድም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል። የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር ነገም ሲቀጥል በክልል ከተሞች ሁለት ጨዋታዎች የሚካሄዱ ይሆናል። በዚሁ መሰረት ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከጎንደር ከተማ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከረፋዱ አምስት ላይ ይጫወታሉ። የዘንድሮው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛው የውድድር ዓመት ሲሆን መከላከያ፣ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከዚህ በፊት የተካሄዱት ውድድሮች አሸናፊ ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም