የወርልድ ቴኮንዷ ፌዴሬሽን በ12ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች ለተሳተፉ ስፖርተኞች የማበረታቻ ሽልማት ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የወርልድ ቴኮንዷ ፌዴሬሽን በ12ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች ለተሳተፉ ስፖርተኞች የማበረታቻ ሽልማት ሰጠ
ኢዜአ ፤ታህሳስ 25/2012 የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኮንዷ ፌዴሬሽን በ12ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች ለተሳተፉ ስፖርተኞች የማበረታቻ ሽልማት አበረከተ። ሽልማቱ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሂዷል። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በሞሮኮ ራባት በተካሄደው 12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከ10 በላይ በሆኑ የስፖርት አይነቶች ተካፍላለች። ከተካፈለችባቸው ስፖርቶች ደግሞ አንዱ ወርልድ ቴኳንዶ ሲሆን አምስት ወንድና አራት ሴት ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን አሳትፋለች። በወርልድ ቴኳንዶ ከተካፈሉት ስፖርተኞች ውስጥ አንድ ወርቅና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማግኘቷም ይታወሳል። በወርልድ ቴኳንዶ ውድድሩ ላይ አትሌት ታሪኩ ግርማ የወርቅ ሜዳሊያና አትሌት ፀባኦት ጎሳዬና ሰለሞን ቱፋ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ ያመጡ ስፖርተኞች ናቸው። የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽኑ በዚህ ውድድር ለተካፈሉ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞችና የህክምና ባለሙያዎች ነው የማበረታቻ ሽልማቱን የሰጡት። በውድድሩ ላይ ወርቅ ላመጣው አትሌት 30 ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል። የነሐስ ሜዳሊያ ላመጡት ደግሞ እያንዳንዳቸው የ20 ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። በተመሳሳይ ሜዳሊያ ያላመጡና በተሳትፎ ብቻ ለተመለሱ ስፖርተኞችም በውድድሩ ላይ እንዳሳዩት ብቃት የስድስት ሺህ እና የሶስት ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥተዋል። በተመሳሳይ ለቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አዲሱ ኡርጌሳ 30 ሺህ ብር የተሰጠ ሲሆን ለምክትል አሰልጣኟ ምህረት ከድር፣ ለረዳት አሰልጣኟ ማርሸት ዘውዱ፣ ለቡድን መሪውና ለህክምና ባለሙያዎችም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።