ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገር ሰላምንና አንድነትን ከማረጋገጥ አኳያ አንድ ዓይነት አቋም ልንይዝ ይገባል - ፓርቲዎች

ኢዜአ ታህሳስ 25/2012 የአገር ሰላምንና አንድነትን ከማረጋገጥ አኳያ አንድ ዓይነት አቋም በመያዝ ለቀጣዩ ምርጫ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ። ኢዜአ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የአገር ሰላምን ለመጠበቅ የተገባውን ቃል ከማክበር አኳያ በተግባር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል።

የፓርቲዎቹ አመራር አባላት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከምርጫና ሌሎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በፊት ሰላምና አንድነትን በማስቀደም በተገባው ቃል መሰረት ሁሉም አብሮ እየተንቀሳቀሰ አይደለም።

በተለይም አንዳንድ ፓርቲዎች ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የገቡትን ቃል እየዘነጉ መሆኑን አመልክተው፤ ከአሁን በፊት "ህዝባዊ ጭቆና ያደርሳሉ ብለው ከሚኮንኗቸው አካላት "ጋር የመወገን፣ አንዳንዶች ደግሞ ዝምታን የመምረጥ አዝማሚያ እንደሚታይባቸው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን ከተካሄዱት ምርጫዎች ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው ምርጫ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ጠቁመው፤ ለዚህ ምክንያቱ የአገሪቷ ወቅታዊ የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ ውጤቱ ያማረ እንዲሆን ፓርቲዎች ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላምና መግባባትን የማምጣት "ሃላፊነታችንን መወጣት አለበን" ሲሉ ገልጸዋል።

"ሰላም የሁላችንም ጉዳይ ነው" ያሉት የፓርቲ አመራር አባላት፤ በተለይም በየክልሉ የሚገኙ ብሄራዊ ፓርቲዎች በየአካባቢያቸው የሰላም ኮንፍረንስ በማካሄድ መረጋጋትን ከመፍጠር አኳያ ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው ነው ያመለከቱት።

የምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የህግ ክፍል ሃላፊ አቶ አስፋቸው አለሜ"አልፎ አልፎ የሚነሱት ግጭቶች በሃይማኖት በብሄር የሚነሱት ግጭቶች አሉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እነዚህንግጭቶች ለማስወገድ ከመንግስት ጋር የፖለቲካ ፓርቲዎች እጅ ለእጅ መያያዝ ይገባቸዋል።" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ኮንግረስ ሊቀ መንበር አቶ ገረሱ ገሳ በበኩላቸው

" በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከልም፣ በተለያዬ ማህበረሰባት አካባቢም፣ በብሄር ብሄረሰቦች መካከልም ሌሎችም አካላት መካከል፣ የጎሪጥ መተያዬቱ ቀርቶ ሰላም መምጣት ማምጣት አለብን" ነው ያሉት፡፡

"ሰላም በቃላት ብቻ አይመጣም በተግባር ልንሰራ ይገባል" ያሉት ፓርቲዎቹ፤ በተለያዩ አካባቢዎች መድረክ እየፈጠሩ ህዝብ በማወያየት ተግባር ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

 "በምኞት ሰላም ሰላም ሰላም በማለት ብቻ ሰላም አይመጣም ወርዶ መስራት ይጠይቃል፣ ዴት ሰላሙን መጠበቅ አለበት፣ ታሪኩን እንዴት መጠበቅ አለበት የሚለው ነው"  ያሉት የመኢአድ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ናቸው፡፡

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ "በኛ በኩል ህዝቡን በመቀስቀስ ችግር እያለብንም እየፈታን ህዝቡን በመቀስቀስና በሰላሙ በሰላሙ ሂደት እንዲራመድ እያደረግን ነው " ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም