የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ የመዲናዋ እድሮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ የመዲናዋ እድሮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ
ኢዜአ ፤ታህሳስ 25/2012 የታላቁ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ እድሮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከመዲናዋ እድሮች ምክር ቤት ጋር በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳትፎና ሂደት ዙሪያ መክሯል። በውይይቱ የተገኙት የእድሮች ምክር ቤቱ አባላት እንደገለጹት በእድሩ ከሚያከናውኑት መደበኛ ተግባራት በተጨማሪ ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። የአዲስ አበባ እድሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ታምራት ገብረማሪያም እንደገለጹት ከእድር ሥራው ጎን ለጎን በልማት ተግበራት ማህበራዊ ኃላፊነትን እየተወጡ ነው። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጀምሮ እስካሁን የፋይናንስና የሞራል ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጉ እድሮች መኖራቸውን ገልጸው ከ3 ሺህ ብር ጀምሮ እንደየአቅማቸው ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል። የህዳሴው ግድብ ግንባታም እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ማህበረሰቡም በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድም ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ሌላዋ የእድር አባል ወይዘሮ አስቴር ለማ በሰጡት አስተያየት እርሳቸው ባሉበት እድርም ከ3 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንና በግላቸውም በየጊዜው ከደሞዛቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቁ ቢያሳዝናቸውም ግድቡ ሲጀመር እንደነበረው ተሳትፎ ግለቱን ጠብቆ እስኪጠናቀቅ ድረስም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሚናረጉት ደግሞ አቶ ደርሶ ዝናቡ ናቸው። ኢትዮጵያውያን የማይጨርሱትን አይጀምሩም፤ ከጀመሩን ከግብ እንደሚያደርሱ የቅድመ አያቶቻችንና አባቶቻችን ታሪክ ያስረዳናል፤ በመሆኑም ሁሉም ማህበረሰብ በመተባበር የግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅ አለበት ብለዋል። ማህበረሰቡም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ የአገሪቷን ሰላም ጠብቆ ግድቡን ለማጠናቀቅ መረባረብ ይገባናል ብለዋል። በሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እየተከናወነ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ ግንባታው 70 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን የሚናገሩት የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን ናቸው። የግንባታው ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስም የፋይናንስ ድጋፍ የሚያስፈልግ በመሆኑ ማህበረሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። የግንበታው ሂደት በስድስት ኮንትራክተሮች እየተከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ኢንጁነር ኤፍሬም፤ የሲቪል ሥራው 85 በመቶ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል 29 በመቶ እንዲሁም የብረታብረት ስራው ደግሞ 15 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል። በአጠቃላይ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት ግን 70 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። በቀጣይ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ግድቡ የቅድመ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ጠቅሰው በ2015 ዓ.ም ሙሉው የግድቡ ስራ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።