ቀጥታ፡

ሴቶችን ያካተተ አገር አቀፍ ጥምረት ተመሰረተ

 ኢዜአ ታህሳስ 25/2012 ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ሴቶችን ያካተተና ‘ሴቶች ለሰላም’ የተሰኘው አገር አቀፍ ጥምረት መመስረቱን የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ። ጉባኤው  ከኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን የእርዳታ ድርጅት ጋር በመሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ሴቶችን ያሳተፈና 'ሴቶች ለሰላም ያላቸው ሚና' ላይ ያተኮረ ውይይት በአዳማ ከተማ አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ሴቶች እንደተናገሩትም ሴቶች በሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ የድርሻቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን እድል አያገኙም።።

በተለያየ መልኩ የተቋቋሙ የሴቶች አደረጃጀቶችም የፖለቲከኞች መሳሪያ ከመሆን ያለፈ ሚና የላቸውም ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሴቶች በሰላም ግንባታ ሂደት የሚጠበቅባቸውን ስራዎች ለማከናወን የሚያስችላቸውን ቋሚ መድረክ ማቋቋም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በዚሁ መሰረት ከህግ ባለሙያዎች ማህበር፣ ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት፣ ከሴቶች ፌደሬሽን፣ ከመምህራን ማህበር፣ ከኃይማኖት ተቋማት ጉባኤና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተውጣጡ ሴቶችን ያካተተ ጥምረት ተመስርቷል።

በጉባኤው የሴቶች፣ ወጣቶችና ልጆች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ገና  እንደተናገሩት የጥምረቱ አላማ ሴቶችን በማደራጀትና በማብቃት በሙሉ አቅማቸው በአገሪቷ የሰላም ግንባታ ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።

በአገሪቷ የሚከሰቱ ግጭቶችን ከመከላከል ችግሩን እስከመፍታት ባለው ሂደትም የሴቶችን ተሳትፎ ማጎልበትና ሌሎች አላማዎችንም ጠቅሰዋል።

በፖለቲከኞች መካከል የሚታዩ ውጥረቶች ተወግደው ወደ ውይይት እንዲመጡም ከኃይማኖት ተቋማትና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር መስራት ከጥምረቱ ኃላፊነቶችና ተግባራት መካከል መሆኑንም ወይዘሮ ጥሩወርቅ ጠቁመዋል።

በህብረተሰቡ መካከል ግጭትን የሚቀሰቅሱ ሁኔታዎችን በንቃት በመከታተል ግጭትን የመከላከል ሚናን መወጣት፣ ለፍትህ አካላት ማሳወቅና ትምህርታዊ መድረኮችን የማዘጋጀት ስራዎችም በጥምረቱ እንደሚከናወኑ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም