ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዢያሜን ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዢያሜን ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝተዋል

ታህሳስ 25/2012 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነገ በቻይና በሚካሄደው የዢያሜን ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝተዋል። የዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶን በ2020 በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ተስጥቷቸው ከሚካሄዱ ውድድሮች የመጀመሪያው ነው። በወንድ ያለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት የዢያሜን ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር አሸናፊ የሆነው አትሌት ደጀኔ የነገውንም ውድድር የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ተሰጥቶታል። የ25 ዓመቱ አትሌት እ.አ.አ በ2019 በአሜሪካ በተካሄደው የቺካጎ ማራቶን 2 ሰአት ከ5 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ ሁለተኛ በወጣበት ውድድር በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱን ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው። በነገው ውድድር እ.አ.አ በ2015 በኬንያዊው አትሌት ሞሰስ ሞሶፕ 2 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ19 ሴኮንድ የተያዘውን የቦታውን ክብረ ወሰን ለማሻሻል እንደሚሮጥ የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያመለክታል። በቅድመ ወድድር ዘገባው የዓለም አትሌቲክስ አትሌት ደጀኔ ቁመታሙና ባለ ረጅም እግሩ አትሌት ሲል የገለጸው ሲሆን ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም 26ኛ ዓመቱን እንደሚደፍንም አስታውቋል። አትሌት ደጀኔ የነገውን ውድድር ካሸነፈ ለሶስተኛ ጊዜ የዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶን አሸናፊ መሆን ይችላል። አትሌት ሹራ ቂጣታ በዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶን ለሶስተኛ ጊዜ ለማሸነፍ የሚሮጥ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሲሆን እ.አ.አ በ2018 በተካሄደው የለንደን ማራቶን 2ሰአት ከ4ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰአት አስመዝግቧል። የሞሮኮና የኬንያ አትሌቶች የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዋነኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎም ይጠበቃል። በሴቶች ደግሞ የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ አትሌት መዲና ደሜ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝታለች። የ22 ዓመቷ አትሌት ባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ስትሆን 2ሰአት ከ27 ደቂቃ ከ25 ሴኮንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷ ሆኖ ተመዝግቦላታል። ሌላኛው አትሌት የብርጉዋል መለሰ 2ሰአት ከ19 ደቂቃ ከ32 ሴኮንድ ያለት ሲሆን በነገው ውድድር ካሉ ሴት አዋቂ አትሌቶች የተሻለ የግል ምርጥ ሰአት አላት። የአትሌት መዲና ዋነኛ ተፎካካሪም ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል። አትሌት አፈራ ጎዳፋይ እና አትሌት ህይወት አያሌው በውደድሩ የሚሳተፉ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። የቤላሩስ፣ቻይናና ኬንያ አትሌቶች የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑም የዓለም አትሌቲክስ ዘገባ ያመለክታል። የዘንድሮው የዢያሜን ዓለም አቀፍ ማራቶን ለ18ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው።