በአማራ ክልል የነዳጅ ሃብት በቁጠባ ለተጠቃሚዎች ለማዳረስ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የነዳጅ ሃብት በቁጠባ ለተጠቃሚዎች ለማዳረስ እየሰራ ነው
ኢዜአ፤ ታህሳስ 24/2012 በመንግስት ድጎማ እየቀረበ ያለውን የነዳጅ ሃብት በቁጠባ ለተጠቃሚዎች ለማዳረስ እየሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ። በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ የተከሰተውን እጥረትና መፍትሄው ዙሪያ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተካሄዷል። የቢሮው ኃላፊው አቶ ብርሃኑ ጣዕምያለው እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ እየታየ ያለው እጥረት የክልሉንም ሆነ የሀገሪቱን ዕድገት እየተገዳደረ ነው። የነዳጅ ፍላጎትና አቅርቦት ችግር በዘላቂነት እስኪፈታም ወደ ክልሉ የገባውን የነዳጅ ሃብት በቁጠባ መጠቀም የሚያስችል አሰራር ያስፈልጋል። በዚህም በአፈፃጸም በኩል የሚታዩ ችግሮችን በተደራጀ አግባብ ለማተካከልና ለማረምም በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። ለነዳጅ እጥረቱ ዋነኛው ምክንያት የሆነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የአቅርቦትና ህገወጥ ንግድ ተጠቃሾች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁናቸው። አቶ ተዋቸው እንዳሉት በአማራ ክልል ከሚገኙት 202 የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ 173 ብቻ ከ90ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ሌሎቹ በብልሽት ምክንያት የማይሰሩ ናቸው። አሁን ላይ ደግሞ በተፈጠረው የነዳጅ አቅርቦት ችግር ምክንያት 38 የሚሆኑት ማደያዎች አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውንም ጠቁመዋል። "በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይም ያለንግድ ፈቃድ ነዳጅ ማዘዋወር፣ ከመንግስት ተመን ዋጋ በላይ መሸጥ፣ የነዳጅ ልኬታ ማጭበርበር፣ ላልተፈቀደላቸው በሌሊት እንዲገዙ መደረግ ተጠቃሾች ችግሮች ናቸው "ብለዋል። በተጨማሪም የመንገድ ላይ የነዳጅ ቅሸባና የጥቁር ገበያ ሽያጭ፣ እንዲሁም በጂቡቲ ወደብ ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ለረጅም ጊዜ ቆመው ወረፋ መጠበቅ ሌላው ተግዳሮት ነው። "ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ማደያዎች ለተጠቃሚዎች በኩፖን እንዲያሰራጩ ማድረግ፣ ነዳጅ በሚያጓጉዙ ቦቴዎች ላይ ጂፒኤስ በመግጠም የክትትልና ቁጥጥር ስራ ማጠናከር ያስፈልጋል " ሲሉ ጠቁመዋል። በክልሉ ማደያዎችንና የቦቲዎችን ቁጥር በቀጣይ በማሳደግ እጥረቱን ለማስተካከል ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ሌሎች ከሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው። የስርጭት አግባቡን ለማስተካከልና ህገ ወጦችን ለመቆጣጠርም ከሰላምና ደህንነት፣ ከገቢዎችና ከአቃቤ ህግ መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ ከዘጠኝ ቢሮዎች የተውጣጣ የነዳጅ ተቆጣጣሪ ግብረ ኃይልም ተቋቁሟል። ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመጡት የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ጥሩ ስራ ተገኘ በሰጡት አስተያየት ለነዳጅ እጥረቱ መከሰት አየር በአየር የሚሸጠውን ነዳጅ አሰራር በመዘርጋት መቆጣጠር እንደሚገባ አመልክተዋል። "ከመስመር ውጭ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች እንዳያዘዋወሩ መቆጣጠርም የሁላችንም ኃላፊነት ነው " ብለዋል። ለግማሽ ቀን በተካሄደው ውይይት ከንግድ ቢሮና ሌሎች ተቋማት የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።