የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን የሚያዘምኑ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ማኑዋሎች ይፋ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን የሚያዘምኑ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ማኑዋሎች ይፋ ሆኑ
ኢዜአ፤ ታህሳስ 24/2012 በኮንስትራሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ በዘልማድ የሚከናወነውን የፕሮጀክት ማኔጅመንት አሰራሮችን የሚያዘምኑ 18 ማኑዋሎች ይፋ ተደረጉ። 'ተወዳዳሪና አገር በቀል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለኢትዮጵያ ብልጽግና' በሚል መሪ ቃል ትናንት የተጀመረው የንቅናቄ ኮንፈረንስ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል። ኮንፈረንሱ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመለየትና የዘርፉን ልማት ለማፋጠን መደላድል መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክሯል። በኮንፈረንሱ የዛሬው ውሎ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት አሰራርን ወደ ዘመናዊ የሚያሸጋግሩ 18 ማኑዋሎች ይፋ ተደርገዋል። እንዲሁም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት የኦንላይን ስልጠና፣ የግንባታ መረጃ ሞዴልና የኮንስትራክሽን ግንባታ ምርታማነት ባህል የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አስመሮም ታደሰ በተለይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት የመፈጸም አቅምን የሚያሳድጉ 18 ማኑዋሎች ከዛሬ ጀምሮ በስራ ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል። ማንዋሎቹ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ ከተደረጉ በኋላ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነት የሚገመግም ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ በቅርቡ እንደሚቋቋም አመልክተዋል። እንደ አቶ አስምሮም ገለጻ፤ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት የሀሳብ፣ የዕቅድ፣ የትግበራ፣ የክትትልና ግምገማ እንዲሁም የማጠናቀቂያ ዑደቶች አሉት። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች በአብዛኛው የዕቅድ ጊዜ ሳይኖራቸው እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። 48 በመቶ የሚሆነው የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት የዕቅድና ዲዛይን ስራዎች የሚከናወኑበት ነው ብለዋል። ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የጊዜና የገንዘብ ወጪ የሚጠይቁት በዝግጅት ምዕራፍ መከናወን የሚገባቸው ጉዳዮች ሳይከናወኑ በመቅረታቸው እንደሆነም አቶ አስምሮም አብራርተዋል። በኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ የሚስተዋሉ የአፈጻጸም ችግሮችን ለማስወገድም ማኑዋሎቹ በስራ ላይ እንዲውሉ የአስገዳጅ ህግ በተያዘው ዓመት እንደሚወጣም ጠቁመዋል። ማንዋሎቹ የግንባታ ወጪ አስተዳደር፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የተግባቦት፣ የተዓማኒነት፣ የግዢ፣ የደህንነት፣ የጤናማ አካባቢ፣ የግንባታ ግብዓትና መሳሪያዎች አጠቃቀምን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ መያዛቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በማኑዋሎቹ ዝግጅት ላይ የተሳተፉት ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቅአለ በበኩላቸው ማኑዋሎቹ በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ የሚታዩ የእውቀት ክፍተቶችን የሚሞሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። እንደ ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ማብራሪያ ማንዋሎቹ መሰረታዊ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ተግባራት የሆኑትን የዕቅድ፣ የትግበራ፣ የክትትልና ግምገማ ስራዎች እንዲሁም የፕሮጀክት መጠንሰሻና ማጠናቀቂያ ሂደቶች ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲከተል የሚያደርጉ ናቸው። በፕሮጀክት ጥንሰሳ ወቅት የኮንስትራክሽ ባለሙያዎች ተሳትፎ ዝቅተኛ በመሆኑም የግንባታ ጊዜና ዋጋ ትመና ላይ በትክክል ማስቀመጥ ላይ ችግር እንደነበረም አብራርተዋል። ''ማንዋሎቹ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች በፕሮጀክት ጥንሰሳ ወቅት ምን ዓይነት ተሳትፎ ቢኖራቸው ትክክለኛውን የግንባታ ጊዜና ዋጋ ማስቀመጥ ይቻላል ለሚለውም ምላሽ ይሰጣሉ'' ብለዋል። ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረጉት ማኑዋሎቹ በኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ዘንድ በትክክል በስራ ላይ ከዋሉ የአገሪቷ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በስርዓት እንደሚመራ ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ገልጸዋል። ይፋ የተደረጉት 18 የፕሮጀክት ማኔጅመንት ማኑዋሎቹ ለዘጠኙ ክልሎችና ለሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የኮንስትራክሽን ቢሮዎች ተሰጥተዋል። እንዲሁም በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ላሉ የሙያ ማህበራት እና ዩኒቨርሲቲዎችም ተበርክቷል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መዘግየት፣ ከጨረታ ውጭ ተጨማሪ ክፍያን በመጠየቅ ለኪሳራ መዳረግን ጨምሮ አያሌ የህግ፣ የአሰራርና የአቅም ችግሮች እንዳሉበት በኮንፈረንሱ ተመልክቷል። ለኢንዱስትሪው አፈፃፀም እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች ጨምሮ አጠቃላይ ተግዳሮቶችን መለየትና የመፍትሄ ሀሳቦች ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ተሰንዝረዋል።