ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ ሰበታ ከተማ ወላይታ ድቻን አሸነፈ

ኢዜአ ታህሳስ 24/2012 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ወላይታ ድቻን 1 ለ 0 አሸንፏል። ውጤቱን ተከትሎ ሰበታ ከተማ በሊጉ ሰባት ደረጃዎችን አሻሽሏል። በስታዲየም ግንባታ ምክንያት ሰበታ ከተማ የሜዳ ጨዋታዎቹን በአዲስ አበባ ስታዲየም እያደረገ ይገኛል። ሰበታ ዛሬም በሜዳው ባደረገው ጨዋታ ፍጹም ገብረማርያም ከእረፍት በፊት ባስቆጠራት የፍጹም ቅጣት ግብ ወላይታ ድቻን 1 ለ 0 አሸንፏል። ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ በአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ የመጀመሪያ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ሰበታ ከተማ ውጤቱን ተከትሎ ነጥቡን ወደ ስምንት በማሳደግ ከነበረበት 13 ደረጃ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል። በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ካሸነፈ በኋላ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። የዛሬውን ውጤት ተከትሎ ወላይታ ድቻ በአምስት ነጥብ ከነበረበት 12ኛ ደረጃ ወደ 13ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ቀጥለው ይካሄዳሉ። ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘውን ሀድያ ሆሳዕናን ያስተናግዳል። በክልል ከተሞች በትግራይ ስታዲየም የሊጉ መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሀዋሳ ከተማ፣ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከባህርዳር ከተማ፣በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር፣ በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማና በዝዋይ ሼር ኢትዮጵያ ሜዳ ወልቂጤ ከተማ ከስሑል ሽረ ጋር በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምናው የሊጉ አሸናፊ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም