ኢትዮጵያዊያኑ ኢንተርናሽናል ዳኞች ከፊፋ የተላከላቸውን ባጅ ተረከቡ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያኑ ኢንተርናሽናል ዳኞች ከፊፋ የተላከላቸውን ባጅ ተረከቡ
ታህሳስ 24/2012 21 ኢትዮጵያዊያን ኢንተርናሽናል ዳኞች ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፊፋ የተላከላቸውን ባጅ ዛሬ በተካሄደ ስነ ስርዓት በይፋ ተረክበዋል። ኢትዮጵያ ያሏትን ኢንተርናሽናል የእግር ኳስ ዳኞች ከማሳደግ አኳያ ብዙ የቤት ስራ እንደሚጠብቃት ተገልጿል። ዛሬ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጃቸውን የተረከቡት ዳኞች እ.አ.አ በ2020 ፊፋ በሚያካሂዳቸውና እውቅና በሰጣቸው ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውደድሮች ላይ ያጫውታሉ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ፈተና ያለፉ ዳኞች ፌዴሬሽኑ የስም ዝርዝራቸውን ለፊፋ ልኮ ነበር። የፊፋ የዳኞች ኮሚቴ ባደረገው ማጣራትና ግምገማም ለ21 ኢትዮጵያዊያን ኢንተርናሽናል ዳኞች ባጅ ልኳል። ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ፣ በላይ ታደሰ፣ ቴዎድሮስ ምትኩ፣ ብሩክ የማነብርሃን፣ ለሚ ንጉሴ፣ አማኑኤል ኃይለስላሴና ዳኛ ሃይለየሱስ ባዘዘው ባጅ ያገኙ ዳኞች ናቸው። ኢንተርናሽናል ዳኛ ክንዴ ሙሴ፣ ተመስገን ሳሙኤል፣ ትግል ግዛው፣ ሸዋንግዛው ተባባል፣ ፋሲካ የኋላሸት እና ይበቃል ደሳለኝ ደግሞ የኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ባጅ አግኝተዋል። ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ፣ አስናቀች ገብሬ፣ ዳኛ ፀሐይነሽ አበበና ኢንተርናሽናል ዳኛ መደብ ወንድሙም የኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባጅ ያገኙ ሴት ዳኞች ናቸው። ኢንተርናሽናል ዳኛ ወይንሸት አበራ፣ ወጋየሁ ዘውዴ፣ ይልፋሸዋ ዘውዴ እና ብርቱካን ማሞም የኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ባጅ አግኝተዋል። ኢንተርናሽናል ዳኛ ፋሲካ የኋላሸትና ኢንተርናሽናል ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ የኢንተርናሽናል ዳኝነት ባጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙ ሲሆን የተቀሩት 19ኙ ነባር ዳኞች ናቸው። በወንድ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ዳዊት አሳምነው፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞች ኃይለራጉኤል ወልዳይ፣ ክንፈ ይልማና በላቸው ይታየው፤ በሴት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አዜብ አያሌው እ.አ.አ. በ2019 ኢንተርናሽናል የዳኝነት ባጅ አግኝተው የነበሩና ዘንድሮ ባጁን ያላገኙ ዳኞች ናቸው። ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ አስናቀች ገብሬ ዳኞቹ ያገኙት ኢንተርናሽናል ባጅ የጠንካራ ስራ፣ ልፋትና ድካም ውጤት ነው ብላለች። ፊፋ በሰጠኝ እውቅና ኢትዮጵያን ወክዬ በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች በጥሩ ብቃትና ስነ ምግባር ለማጫወት በትጋት እሰራለሁ ስትልም ገልጻለች። ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ባገኘነው ኢንተርናሽናል የዳኝነት ባጅ ደስተኞች ብንሆንም ያሉንን ዳኞች ቁጥር ማሳደግ ላይ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብሏል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ከፍተኛ ትዕግስት በሚጠይቀውና ፈታኝ በሆነው የዳኝነት ሙያ መልካም በመስራት ባጅ ላገኙ ዳኞች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ቁጥርና ከሚካሄዱ የሊግ ውድድሮች ብዛት አንጻር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሏት የዳኞች ቁጥር አነስተኛ የሚባል እንደሆነ ገልጸዋል። ኢንተርናሽናል ዳኞች ከነሱ በታች ላሉ ዳኞች ያለፉበትን መንገድና መስመር ማስተማር እንደሚገባቸውም ነው አቶ ኢሳያስ ያሳሰቡት። እ.አ.አ በ2021 ኢንተርናሽናል የዳኝነት ባጅ ያላቸውን ዳኞች ቁጥር ለመጨመር ከወዲሁ ጠንካራ ስራና ዝግጅት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በፊፋ 22 ኢንተርናሽናል ባጅ የማግኘት ኮታ አላት። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ለዳኞቹ ከፊፋ የተላከውን ባጅ አበርክተዋል።