ቀጥታ፡

ልማት ባንክ "ብድር ከማቅረብ ይልቅ የሰጠሁትን መሰብሰብ ላይ ትኩረት አድርጊያለሁ" አለ

ኢዜአ፤ ታህሳስ 24/2012 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እርሻና ኢንዱስትሪን ጨምሮ ለሌሎች ዘርፎች እድገት ያበደረው 16 ቢሊዬን ብር 'የተበላሸና አጠራጣሪ' የብድር ክምችት እንደሆነበት ገለጸ:: በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዮች ቋሚ ኮሚቴ ስር የሚገኘው የመንግስት ልማት ድርጅቶች ንኡስ ኮሚቴ የተመራ ቡድን የልማት ባንክ ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት የባንኩ የአምስት ወራት ሪፖርት ሲቀርብ እንደተገለጸው፤ በአሁኑ ወቅት ባንኩ ብድር ከማቅረብ ይልቅ የሰጠሁትን መሰብሰብ ላይ ትኩረት አድርጓል። ከዚህ በፊት የልማት ባንኩ የእርሻና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለመደገፍ የሰጣቸው ብድሮች አሳሳቢ በሆነ መልኩ የተባለሽና አጠራጣሪ ከመሆናቸውም በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስምንት ቢሊዬን ወደ 16 ቢሊዬን ብር አድጓል። የልማት ባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ እንደሚሉት፤ በቅርብ ዓመታት የአገሪቷን እርሻ ስራ ለማሻሻል 6 ነጥብ 3 ቢሊዬን ብር በብድር መልክ ተለቋል። ከዚያ ውስጥ 5 ነጥብ 3 ቢሊዮኑ የተባለሽ ብድር ሆኗል። ባለሀብቶቹ በጎንደር አካባቢ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ አካባቢዎች የእርሻ ኢንቨስትመንት ስራ ለመስራት የተበደሩ መሆናቸውን ነው ያስታወሱት። በጋምቤላ ብሄራዊ ክልል ብቻ ብድር ከወሰዱት 154 ባሃብቶች መካከል 66ቱ አገር ጥለው የጠፉ ሲሆን፤ 24ቱ ብቻ በአግባቡ ስራቸውን እያከናወኑ ናቸው። በዚሁ ክልል የተሰማሩ ባለሃብቶች ከ 2 ነጥብ 34 ቢሊዬን ብር በላይ መበደራቸውን አስታውሰው፤ አብዛኞቹ "በስራቸውም ውጤታማ አልሆኑም፤ ብድሩም በተበላሸ ተይዟ" ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የብድር አመላለስ ችግር ውስጥ ገብተዋል፤ ኪሳራ አስከትለዋል። ለአብነትም በአዳማ ከተማ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማራው 'ኤልሴ አዲስ' የተባለ ኩባንያ "800 ሚሊዬን ብር ተበድሮ መጨረሻ ላይ ፋብሪካውን ጥሎ ጠፍቷል" ብለዋል። በተመሳሳይ ለገጣፎ አካበቢ አንድ ኩባንያ 250 ሚሊዬን ብር ተበድሮ ጥሎ የጠፋ መሆኑን አውስተው፤ ባንኩ ተረክቦ ሲያስተዳድረው ቆይቶ እንደተዘጋም አብራርተዋል። ሰበታ የሚገኘውና 4ሺ 500 ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው 'አይካ አዲስ' ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካም ሦስት ቢሊዬን ብር ተበድሮ ባለቤቶቹ ጥለውት በመጥፋታቸው ባንኩ እያስተዳደረው ይገኛል። ፋብሪካው ባለው ወቅታዊ ገበያ ሁለት ቢሊዬን ገደማ እንደሚያወጣ መገመቱን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ''ባንኩ ተመሳሳይ 11 ድርጅቶችን ተረክቦ እያስተዳደረ ይገኛል'' ብለዋል። ''የተባለሸ ወይም አጠራጣሪ ብድር ማለት ሙሉ በሙሉ የባከነ ወይም የጠፋ ተድርጎ መወሰድ የለበትም'' በማለትም ፕሬዚዳንቱ ይገልጻሉ። ከዚህ ጎን ለጎን በአገሪቷ ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ብድር ከወሰዱ ከ462 ኢንቨስትመቶች መካከል 37 ለውድመት መዳረጋቸውን አመልክተዋል። የልማት ባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ አለማየሁ ደግሞ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ባንኩ ከችግር ለመውጣት ፖለሲውን ጭምር አሻሽሎ ወደ ስራ ገብቷል። ባንኩን ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረጉት ከብድር አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ብድር ማስመለስ ድረስ የተዘረጋ የአሰራር ብልሽት መሆኑን ተናግረዋል። ከባንኩ ውጪም ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት መሬት ሲውስዱ ትክክል ባለሆነ መልኩ መሆኑን ገልጸው፤ ''ሆን ብለው የባንኩን ገንዘብ ለመውስድ የተሰማሩም ነበሩ'' ብለዋል። የባለሃብቶችን የካፒታል አቅም ባግባቡ ማረጋገጥ፣ ከዚህ በፊት ይፈቀድ የነበረውን በአሮጌ ቁሰቁሶች ፋብሪካ የመገንባት ሂደት እንዲቆም መደረጉንም ጠቁመዋል። የልማት ባንኩ ፐሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በተጨማሪ ጥፋተኞችን መቆጣጠርን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ ጥፋተኞችን በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተከናወነ ነው። እስካሁንም ሶስት ባለሃብቶች ለሕግ የቀረቡ ሲሆን፤ አምስት የባንኩ ሰራተኞችም ተጠያቂ ሆነው ዘጠኙ  የዲሲፒሊን እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል። 16 ማሽነሪ አቅራቢዎችም ከባንኩ 78 ሚሊዬን ብር ተበድረው ማሽኖቹ ስላልገቡ እነርሱም በሕግ ተጠያቂ መደረጋቸውን ገልጸዋል። ጥፋተኞችን ተጠያቂ የማድረጉ ስራ አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው፤ ''እስካሁን የዘገየው ትክክለኛ ማስረጃ መጠናቀር በማስፈለጉ ነው'' ይላሉ አቶ ኃይለየሱስ። የተበላሹ ወይም አጠራጣሪ ብድሮችን በማስመለስ ረገድም ባለፉት አምስት ወራት 202 ሚሊዬን ብር ገደማ መመለሱን አውስተዋል። የንኡስ ኮሚቴው መሪ ወይዘሮ ሰራ አብዲ እንደገለጹት፤ ባንኩ ከገባበት ችግር ለመውጣት እያደረገ ያለው ጥረ የሚበራታታ ነው። ከምንም በላይ ከችግሩ ለመውጣትና የተበላሽ ብድር ለማስመለስ የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናከር አሳስበዋል። ባንኩ በ1901 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ በተለያዩ ወቅቶች ስሙን ቢቀያይርም ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኖታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም