የሴት አደረጃጀቶች ማህበረሰብ ተኮር የሰላም ተግባራትን እንዲያከናውኑ እየተሰራ ነው...የሠላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሴት አደረጃጀቶች ማህበረሰብ ተኮር የሰላም ተግባራትን እንዲያከናውኑ እየተሰራ ነው...የሠላም ሚኒስቴር
ኢዜአ ታህሳስ 24 /2012 ---የሴት አደረጃጀቶች ማህበረሰብ ተኮር የሰላም ተግባራትን እንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ከ"ጀስትስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሽፕ ኢትዮጵያ" ጋር በመተባበር በሰላም እንዲሁም በግጭት መከላከልና አፈታት ላይ የሴቶችና ወጣቶችን ሚና ለማሳደግ ያዘጋጀው የስልጠና መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በወቅቱ እንደገለጹት ሴቶች ለሁለንተናዊ ሰላምና ፍትህ መስፈን እንዲሁም አለመግባባቶችን ለመፍታት የላቀ ሚና እንዳላቸው በጥናት ተረጋግጧል። ሴቶች ሰላምን ለማስፈን ያላቸውን ድርሻ በመረዳት ሚኒስቴሩ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን እንዲሁም በፌዴራልና ክልል ደረጃ ከሚገኙ የሴት አደረጃጀቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። “እናቶች የሰላም ተምሳሌት ናቸው” በሚል መሪ ቃል ሴቶችን በማደራጀት በሁሉም ክልልች፣ የከተማ አስተዳደሮችና ዩኒቨርሲቲዎች ተዘዋውረው ስለሰላም አስፈላጊነት እንዲሰብኩ ጥረት መደረጉንም ለአብነት ጠቅሰዋል። የሰላም መስበክ እንቅስቃሴው በህብረተሰቡ ውስጥ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣና ግጭቶች እየረገቡ እንዲመጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ የተጀመረውን የሰላም ማስፈን ተግባር ለማስፋፋት የሴቶችን አቅምና ክህሎት ለማሳደግ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ወይዘሮ አልማዝ አስታውቀዋል። "በተዘጋጀው የስልጠና መድረክም ብሔራዊ የሴቶች የሰላም ምክር ቤት ይቋቋማል" ብለዋል። የሚቋቋመው ምክር ቤት ሴቶች በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ እንዲሰፍን ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችላቸው መሆኑን አመላክተዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ተወካይ ወይዘሮ አስካለ ለማ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ የሃሳብ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ከማድረግ አንፃር የሴቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። "የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ አንጻር የሴቶችን አስተዋጽኦ ተቋማዊ በሆነ አደረጃጀት ለመምራት የኢትዮጵያ ሴቶች ሰላም ምክር ቤት ለማቋቋም ተወስኗል" ብለዋል። ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ የምክር ቤቱ አባላት በየአካባቢያቸው ሴቶችን በማደራጀትና ትርጉም ያለው የሴቶች ንቅናቄ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። የጀስትስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሽፕ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ በሀገሪቱ ግጭቶችን ለማስወገድ ከመንግስትና ከሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። በሰላም እጦት የመጀመሪያ ተጎጂ ሴቶችና ህጻናት በመሆናቸው ለሰላም ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉ መድረኩ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።