ቀጥታ፡

የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለዋል

ኢዜአ ታህሳስ 24/2012.. የሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ተካሄደዋል። የአቋም መለኪያ ውድድሩ ከትናንት በስቲያ ነው የተጀመረው። ዛሬ በመጀመሪያው ጨዋታ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተጋጥመው ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጋጣሚውን 3 ለ 1 አሸንፏል። ከብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጋር በነበራቸው ጨዋታ የታየባቸውን የአሰራረብና ቦታ አያያዝ ድክመት አስወግደው የቀረቡት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ቀርበዋል። የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ በማሸነፍ ተጋጣሚያቸውን መምራት ቢችሉም ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ልምዱን በመጠቀም ማሸነፍ ችሏል። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የልምድ ማነስ ተሸናፊ ቢያደርገውም የጨዋታ ልምድ እያገኘ ሲመጣ በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን እንደሚችል በዛሬው ጨዋታ አሳይቷል። ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከመጀመሪያው ጨዋታ በተወሰነ መልኩ መዳከም ታይቶበታል። ዛሬ በተካሄደው ሌላ ጨዋታም ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብን በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 0 አሸንፏል። የአንድ ቡድን የበላይነት በታየበት በዚህ ጨዋታ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች የሰበሰበው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጨዋታውን በቀላሉ ማሸነፍ ችሏል። ጌታዘሩ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት አለማድረጉን በሁሉም ስፍራዎች በታየበት ክፍተት በግልጽ ተስተውሏል። እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ሁለት ጊዜ ተሸንፈዋል። ነገ ሁለት ጊዜ የተሸነፉት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ይጫወታሉ። ከነገ በስቲያ ውድድሩ ሲጠናቀቅ ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ30 ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካና ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። በተያያዘ ዜና የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቢል ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በ8፡00 ሠዓት ከመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ከጣና ባህርዳር ከቀኑ በ9፡00 ሠዓት ይጫወታሉ። ሙገር ላይ ከረፋዱ 4፡00 ሠዓት ሙገር ሲሚንቶ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ሶዶ ላይ የሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ ከመከላከያ መጫወት የነበረባቸው ቢሆንም የጨዋታው ሜዳ ለሌላ አገልግሎት በመያዙ ለሌላ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን አስታውቋል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በስምንት ነጥብ ሲመራ፤ ሙገር ሲሚንቶ በሰባት፣ አዲስ አበባ ፖሊስ በስድስት ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን ስምንተኛ ደረጃ ይዟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም