ቀጥታ፡

የወይዘሮ ፍሬወይኒ መብራህቱ ሽልማት ለኢትዮጵያዊያን ሴቶች ትልቅ ኩራት ነው--- ዶክተር አብርሃም ተከስተ

ኢዜአ ታህሳስ 24/2012 የወይዘሮ ፍሬወይኒ መብራህቱ ያገኙት የሲኤን ኤን የ2019 ጀግና የስራ ፈጠራ ሽልማት ለኢትዮጵያዊያን ሴቶች ትልቅ ኩራት መሆኑን በትግራይ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕርግ የንግድና ኢንዱስቱሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብረሀም ተከስተ ገለጹ። የክልሉና መቀሌ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች በጋራ በመሆን ለጀግናዋ  ስራ ፈጣሪ  ፍሬወይኒ መብራህቱ ትላንት የእንኳን ደስ አልዎት ፕሮግራም የእራት ግብዣ አድርገውላቸዋል። በስነስርዓቱ  የተገኙት ዶክተር አብርሃም ተከስተ  እንደተናገሩት የወይዘሮ ፍሬወይኒ መብራህቱ  ሽልማት ለክልሉ ብሎም ለኢትዮጵያዊያን ሴቶች ትልቅ ኩራት ነው። "በዓላማ የፀና  ማሸነፍ እንደሚቻል አሳይታለች"  ያሉት ዶክተር አብርሃም የክልሉ መንግስት ለስራቸው መሳካት ከጎናቸው እንደማይለይ ቃል ገብተዋል። የክልሉ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት አቶ አሰፋ ገብረ ስላሴ በበኩላቸው "ወይዘሮ ፍሬወይኒ ወቅቱ ለሚፈልገው የልማት ጀግንነት የአለም ተምሳልት ሆናለች"ብለዋል። ሴቶች በሁሉም የስራ ዘርፍ ተወዳዳረው ቀዳሚ እንደሚሆኑ የሚያሳይ ውጤት እንደሆነ ጠቅሰው በተለይ የሴቶችን ችግር የሚፈታ የንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ  ዘርፍ ላይ  መሰማራታቸው ልዩ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል። ምርታቸው  የሴቶች  ችግር ፈቺ ሆኖ እንዲቀጥልና በአለም ደረጃ ተወዳዳሪ  እንዲሆኑ   ነጋዴው ማህበረሰብ ከጎናቸው  እንደሚሆን አስታውቀዋል። "መንግስትና የንግዱ ማህበረሰብ ከጎንሽ አለን ስላሉኝ የጀመርኩት ስራ ይበልጥ እንዲሰፋፋ ጉልበት ይሆነኛል "  ተሸላሚዋ ወይዘሮ ፍሬወይኒ መብራህቱ ናቸው ። ምርቱ  እስካሁን ለአንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን  ሴቶች መዳረሱን ጠቁመው  ምርቱን በሁሉም የኢትዮጵያ አከባቢዎች ከማዳረስ ባለፈ በሌሎች ሀገራት ተወዳዳሪ እንዲሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ወይዘሮ ፍሬወይኒ መብራህቱ በሲኤን ኤን  እንደ አውሮፓ  አቆጣጠር የ2019  ጀግና ስራ ፈጣሪ አድረጎ በቅርቡ መሸለማቸው ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም