የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ፖለቲከኞች በሰከነ አግባብ ሊወያዩ ይገባል - ምሁራንና የፓርቲ አመራር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ፖለቲከኞች በሰከነ አግባብ ሊወያዩ ይገባል - ምሁራንና የፓርቲ አመራር አባላት
ኢዜአ፤ ታህሰሳስ 24/2012በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮችን በውይይት መፍታት ከተቻለ ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት የሚያስችል የተመቻቸ ሁኔታ መኖሩን ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ገለጹ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ጋር በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል። በውይይቱ ላይ ከኦሮሚያ የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተገኙት አቶ ታዬ ደንደአ፤ "ልጆቻችን በሠላም የሚኖሩባትና ሁሉም በእኩልነት የሚስተናገዱባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት" ፓርቲያቸው እየሠራ መሆኑን ነው የገለጹት። የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚቻለው ምሁራንና ፖለቲከኞች መርህን ተከትለው እየተደማመጡ መወያየት ሲችሉና መላው ህዝብ ሙሉ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጡ መሆኑንም ተወያዮቹ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ "ብሩሕ ተስፋና ሥጋት ነው" በማለት በሁለት መልኩ የሚገልጹት ደግሞ የሕግ ምሁሩ ዶክተር ዮናስ ተስፋ ናቸው። አገሪቷን ወደተሻለ አቅጣጫ እየወሰዳት ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ጅምሩ በጥንቃቄ መያዝ እንደላበት ያመለከቱት ዶክተር ዮናስ፤ ምሁራንና ፖለቲከኞች በጥንቃቄ መጓዝ ካልቻሉ ሊከሰት የሚችለው አደጋ "የአሁኑን ትውልድ የታሪክ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው" ይላሉ። ለውጡ ይዞ ስለመጣው ተስፋና ሥጋት የምሁራኑንና የፓርቲ አመራር አባላት አተያይን እንደሚጋሩ የሚጋሩት ደግሞ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ወክለው በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ ናቸው። አቶ ሙሉብርሃን "እኛ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ያለን የፖለቲካ ባህል ደካማ መሆኑ ለውጡ ያመጣውን መልካም አጋጣሚ ሊያጨልምብን ይችላል" የሚል ስጋት አላቸው። እስከ አሁን "የነበርንበት የፖለቲካ ሁኔታ አስቸጋሪና የታፈነ ነበር" የሚሉት የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲን የወከሉት አቶ ታዬ፤ የለውጥ ኃይሉ በአገሪቷ የሁሉም ፖለቲከኞችና ምሁራን ሃሳቦች በነፃ ወደ ገበያ እንዲቀርቡና እንዲደመጡ መድረኩን መክፈቱን አብራርተዋል። 'አገር የሚገነባው ለትውልድ ነው' የሚሉት ተወያዮቹ፤ አገር በተሻለ ሁኔታ ግንብቶ ለቀጣዩ ትውልድ ለማቆየት ፖለቲከኞች ያላቸውን አማራጭ ሃሳብ በነፃነት ለገበያው በማቅረብ ሀሳባቸውን በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።