ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተልዕኮና በልህቀት ለማደራጀት የሚያስችለው ጥናት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተልዕኮና በልህቀት ለማደራጀት የሚያስችለው ጥናት ይፋ ሆነ

ኢዜአ ታህሳስ 24/2012.. ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተልዕኮና በልህቀት ለማደራጀት የሚያስችለው ጥናት ዛሬ ይፋ ሆነ። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተልዕኮና በልህቀት ለማደራጀት የሚያስችለው ጥናት ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ አመራሮችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ይፋ ሆኗል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲዎች ውጤታማ ሊሆኑ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ጥናት ሲደረግ ቆይቷል። ለዚህም የ11 የውጭ አገሮችን ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ የዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ አቅጣጫዎችና በዘርፍ መለያየት በተለይ ከትምህርት ጥራትና አግባብነት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ታምኖበታል። በዚህም መሰረት ስምንት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምርምር፣ 15 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአፕላይድ ሳይንስ፣ 21 የትምህርት ተቋማት አጠቃላይ እንዲሁም ሶስት የትምህርት ተቋማት ደግሞ ስፔሻላይዝድ በሚል ተለይተዋል። እነዚህ የተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች ባላቸው የምርምር ቤተ-ሙከራዎች፣ መሰረተ ልማቶች፣ በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ አቅማቸው፣ በኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም ለግብርና ምርት ማቀነባበር ምቹ ሁኔታ ላይ ያሉትን በማጥናትና መሰረት በማድረግ መለየታቸውን ገልጸዋል። ''ዩኒቨርሲቲዎቹ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግና በግብርና ምርት ማቀነባበር ኢንዱስትሪውን እያገዙ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመነጩና የሚያሳድጉ፣ ብቁ የሰው ሃይል የሚፈጥሩ በመሆን ለኢኮኖሚው እድገት ጉልህ ድርሻ እንዲኖራቸው ይረዳል'' ብለዋል። በመሆኑም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ ተማሪዎች ምደባ፣ የመምህር ቅጥር፣ የግብአትና የበጀት አጠቃቀም የምርምር፣ የአፕላይድ ሳይንስ፣ ስፔሻላይዝድ እንዲሁም አጠቃላይ ተብለው በተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች መሰረት እንደሚሆንም ጠቁመዋል። አዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ሀሮማያ፣ ሀዋሳ፣ አርባምንጭ፣ ባህር ዳር እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ተብለው ተመድበዋል። አክሱም፣ ድሬዳዋ፣ ደብረብርሃን፣ ወሎ፣ አርሲ፣ አሶሳ፣ ዲላ፣ ደብረማርቆስ፣ ኮተቤ፣ ወለጋ፣ ወልቂጤ፣ ጅግጅጋ፣ ወላይታሶዶ፣ ሰመራ እና አምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ የአፕላይድ ሳይንስ ይሆናሉ ተብሏል። አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ደግሞ ስፔሻላይዝድ ተብለው ከተለዩት መካከል ናቸው። መቱ፣ ሚዛን፣ ጋምቤላ፣ ዋቻሞ እና ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አጠቃላይ ትምህርት የሚሰጡ እንደሚሆኑ ተገልጿል። በሌላ በኩል በቀጣይ "students loan fund" በሚል የተማሪዎች የብድር ስርአት ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጿል። ይህም ከፍለው መማር የማይችሉና ሌሎች የማህበራዊ ችግሮች ካሉባቸው ተማሪዎች ውጪ ትምህርት በነጻ የማይሰጥ ሲሆን ሌላው ማንኛውም ተማሪ ከፍሎ ወይም ብድር ወስዶ መማር የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖርም ሚኒስትሯ አክለዋል።